የዮሐንስ ወንጌል 13
13
ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር እንደ አጠበ
1ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን፥ የወደዳቸውን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው። 2እራትም ሲበሉ፥ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካስገባ በኋላ፥ 3ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደሰጠው፥ ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣና ወደ እግዚአብሔርም እንደሚሄድ አውቆ፥ 4ከማእድ ተነሣ፤ ልብሱንም አኖረ፤ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ 5በኋላም በመታጠቢያው ውሃ ጨመረ፤ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ማጠብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ማበስ ጀመረ። 6ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም “ጌታ ሆይ! አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” አለው። 7ኢየሱስም መልሶ “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። 8ጴጥሮስም “የእኔን እግር በጭራሽ አታጥብም” አለው። ኢየሱስም “ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ድርሻ የለህም፤” ብሎ መለሰለት። 9ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! እንግዲያውስ እግሬን ብቻ ሳይሆን፥ እጄንና ራሴንም ጭምር” አለው። 10ኢየሱስም “ሰውነቱን የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፤ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁም አይደላችሁም፤” አለው። 11አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና “ሁላችሁ ንጹሐን አይደላችሁም” አለው።
12 #
ሉቃ. 22፥27። እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? 13እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ ስለሆንኩም መልካም ትናገራላችሁ። 14እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባል። 15እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተም እንዲሁ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። 16#ማቴ. 10፥24፤ ሉቃ. 6፥40፤ ዮሐ. 15፥20።እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም፤ 17ይህንን ስታውቁና ስታደርጉ ብፁዓን ናችሁ። 18#መዝ. 40፥10።ስለ ሁላችሁም አይደለም የምናገረው፤ እኔ የመረጥኋቸውን አውቃለሁ፤ ነገር ግን ቅዱስ መጽሐፍ ‘እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ’ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው። 19አሁን አስቀድሜ የምነግራችሁ፥ በተከሠተ ጊዜ እኔ መሆኔን ታምኑ ዘንድ ነው። 20#ማቴ. 10፥40፤ ማር. 9፥37፤ ሉቃ. 9፥48፤ 10፥16።እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የምልከውን ማንኛውንም ሰው የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።”
ኢየሱስ አሳልፎ ስለ መስጠት
(ማቴ. 26፥20-25፤ ማር. 14፥17-21፤ ሉቃ. 22፥21-23)
21ኢየሱስ ይህን ብሎ በመንፈሱ ተረበሸ፤ እንዲህም ሲል መሰከረ፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ። 22ደቀመዛሙርቱ ስለ ማን እንደ ተናገረ ግራ ገብቶአቸው እርስ በርሳቸው ተያዩ። 23ከደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ይወደው የነበረው አንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ፤ 24ስምዖን ጴጥሮስም በምልክት “ሰለ ማን እንደ ተናገረ ንገረን” አለው። 25እርሱም ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ “ጌታ ሆይ! ማን ነው?” አለው። 26ኢየሱስም “እኔ የእንጀራ ቁራሽ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” ብሎ መለሰለት። ቁራሽም አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ለስምዖን ልጅ ለይሁዳ ሰጠው። 27እርሱም ቁራሹን ከተቀበለ በኋላ ሰይጣን ገባበት። ኢየሱስም “የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ፤” አለው። 28ነገር ግን ስለምን ይህን እንዳለው በማእድ ከተቀመጡት ማንም አላወቀም፤ 29ይሁዳ የገንዘብ ከረጢቱን ይዞ ስለ ነበር፥ አንዳንዶቹ ኢየሱስ “ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ፤ ወይም ለድሆች ምጽዋት ስጥ” ያለው መስሎአቸው ነበርና። 30እርሱም ቁራሹን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው ወጣ፤ ሌሊትም ነበረ።
አዲሱ ትእዛዝ
31ከወጣም በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አሁን የሰው ልጅ ከብሯል፤ በእርሱም እግዚአብሔር ከብሯል፤ 32እግዚአብሔር ስለ እርሱ የከበረ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ደግሞ እርሱን ራሱን ያከብረዋል፤ ወዲያውም ያከብረዋል። 33#ዮሐ. 7፥34።ልጆች ሆይ! ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድም ‘እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም፤’ እንዳልኋቸው፥ አሁን ለእናንተ ደግሞ እላችኋለሁ። 34#ዮሐ. 15፥12፤17፤ 1ዮሐ. 3፥23፤ 2ዮሐ. 1፥5።አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እርሱም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። 35እርስ በርሳችሁ ብትዋድዱ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።”
ጴጥሮስ እንደሚክደው ኢየሱስ አስቀድሞ እንደ ተናገረ
(ማቴ. 26፥31-35፤ ማር. 14፥27-31፤ ሉቃ. 22፥31-34)
36ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ወዴት ትሄዳለህ?” አለው። ኢየሱስም “ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፥ ነገር ግን በኋላ ትከተለኛለህ” ብሎ መለሰለት። 37ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! አሁን ልከተልህ የማልችለው በምን ምክንያት ነው? ነፍሴን እንኳ ስለ አንተ እሰጣለሁ” አለው። 38ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰለት “ነፍስህን ስለ እኔ ትሰጣለህን? እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዶሮ አይጮኽም።”
Айни замон обунашуда:
የዮሐንስ ወንጌል 13: መቅካእኤ
Лаҳзаҳои махсус
Паҳн кунед
Нусха
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in