ኦሪት ዘፍጥረት 16
16
አጋርና እስማኤል
1የአብራም ሚስት ሣራይ ገና ልጅ አልወለደችለትም ነበር፤ ነገር ግን አጋር የምትባል አንዲት ግብጻዊት አገልጋይ ነበረቻት፤ 2ስለዚህ ሣራይ አብራምን “እነሆ፥ እግዚአብሔር ልጅ እንዳልወልድ ከልክሎኛል፤ ወደዚህች ወደ አገልጋዬ ግባ፤ ምናልባት በእርስዋ በኩል ልጅ አገኝ ይሆናል” አለችው። አብራምም ሣራይ ባለችው ነገር ተስማማ። 3ስለዚህ ሣራይ ግብጻዊት የሆነች አገልጋይዋን አጋርን ለአብራም ሚስት እንድትሆነው ሰጠችው። ይህም የሆነው አብራም በከነዓን ዐሥር ዓመት ከኖረ በኋላ ነው። 4አብራም ወደ አጋር ገባ፤ ፀነሰችም፤ አጋር መፅነስዋን ባወቀች ጊዜ በእመቤትዋ ላይ ኮራች፤ ናቀቻትም።
5ሣራይም አብራምን “የደረሰብኝ በደል በአንተ ላይ ይሁን፤ እርስዋን ለአንተ የሰጠሁህ እኔ ራሴ ነኝ፤ እርስዋ ግን መፅነስዋን ካወቀችበት ጊዜ አንሥቶ እኔን መናቅ ጀምራለች፤ አሁንም ከእኔና ከአንተ ጥፋተኛው ማን እንደ ሆነ እግዚአብሔር ይፍረድ!” አለችው።
6አብራምም “መልካም ነው፤ እርስዋ የአንቺ አገልጋይ ስለ ሆነች በቊጥጥርሽ ሥር ናት፤ የፈለግሺውን ነገር አድርጊ” አላት። ከዚህ በኋላ ሣራይ አጋርን እጅግ ስላሠቃየቻት አጋር ከቤት ወጥታ ኰበለለች።
7የእግዚአብሔር መልአክ አጋርን በበረሓ በሚገኘው በአንድ ምንጭ አጠገብ አገኛት፤ ይህም ምንጭ ወደ ሹር በሚወስደው መንገድ ላይ ነበር። 8መልአኩም “የሣራይ አገልጋይ አጋር ሆይ፥ ከወዴት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጂአለሽ?” አላት።
እርስዋም “እኔ ከእመቤቴ ከሣራይ ሸሽቼ ነው” አለችው።
9መልአኩም “ወደ እመቤትሽ ተመለሽና አገልግያት” አላት። 10ደግሞም እንዲህ አላት፤ “ማንም ሊቈጥረው እስከማይችል ድረስ ዘርሽን አበዛዋለሁ፤
11እነሆ፥ ፀንሰሻል፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤
እግዚአብሔር የሐዘን ለቅሶሽን ስለ ሰማልሽ
ስሙን እስማኤል ትይዋለሽ። #16፥11 እስማኤል፦ በዕብራይስጥ “እግዚአብሔር ይሰማል” ማለት ነው።
12ነገር ግን እንደ ሜዳ አህያ ይሆናል፤
ሰውን ሁሉ ይቃወማል፤
ሰዎችም እርሱን ይቃወሙታል፤
ዘመዶቹን በመጥላት ተለይቶ ይኖራል።”
13አጋርም “በእርግጥ የሚያየኝን እግዚአብሔርን በዐይኔ አይቼ በሕይወት ኖርሁን?” በማለት ያነጋገራትን ጌታ “ኤልሮኢ” አለችው፤ ትርጒሙም “የሚያየኝ አምላክ” ማለት ነው። 14ስለዚህ ሰዎች በቃዴስና በባሬድ መካከል የሚገኘውን የውሃ ጒድጓድ “ብኤር ላሐይ ሮኢ” ብለው ይጠሩታል፤ ትርጒሙም “ሕያው የሆነውና የሚያየኝ አምላኬ ጒድጓድ” ማለት ነው።
15አጋር ለአብራም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ እርስዋ የወለደችለትንም ልጅ “እስማኤል” ብሎ ስም አወጣለት፤ #ገላ. 4፥22። 16አብራም በዚያን ጊዜ 86 ዓመት ሆኖት ነበር።
Айни замон обунашуда:
ኦሪት ዘፍጥረት 16: አማ05
Лаҳзаҳои махсус
Паҳн кунед
Нусха
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997