የሉቃስ ወንጌል 12
12
ስለ ፈሪሳውያን እርሾ
1 #
ማቴ. 16፥6፤ ማር. 8፥15። በዚያን ጊዜም እጅግ ብዙ ሰዎች እርስ በርሳቸው እስኪረጋገጡ ድረስ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ ይላቸው ጀመረ፥ “አስቀድማችሁ ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ፤ ይኸውም ግብዝነት ነው። 2#ማር. 4፥22፤ ሉቃ. 8፥17። የማይገለጥ የተሰወረ፥ የማይታይም የተሸሸገ የለምና። 3በጨለማ የምትናገሩት በብርሃን ይሰማል፤ በእልፍኝም ውስጥ በጆሮ የምትንሾካሾኩት በሰገነት ይሰበካል። 4ለእናንተ ለወዳጆች እላችኋለሁ፦ ሥጋችሁን የሚገድሉትን አትፍሩአቸው፤ ከዚህም የበለጠ ማድረግ የሚችሉት የላቸውም። 5ነገር ግን፤ የምትፈሩትን አሳያችኋለሁ፤ እናንተስ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ሊጥል ሥልጣን ያለውን ፍሩት፤ አዎ፥ እላችኋለሁ፤ እርሱን ፍሩ። 6አምስት ወፎች በሁለት ሻሚ መሐለቅ ይሸጡ የለምን? ከእነርሱ አንዲቱ ስንኳን በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም። 7የእናንተስ የራስ ጠጕራችሁ ሁሉ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲህ አትፍሩ፤ ከብዙ ወፎች እናንተ ትበልጣላችሁና።
8“እላችኋለሁ፦ በሰው ፊት የሚያምንብኝን ሁሉ እኔም#በግሪኩ “የሰው ልጅም ...” ይላል። በእግዚአብሔር መላእክት ፊት አምነዋለሁ። 9በሰው ፊት የሚክደኝን ግን እኔም በእግዚአብሔር መላእክት ፊት እክደዋለሁ። 10#ማቴ. 12፥32፤ ማር. 3፥29። በሰው ልጅ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ግን በዚህ ዓለምም ሆነ በሚመጣው ዓለም#“በዚህ ዓለምም ሆነ በሚመጣው ዓለም” የሚለው በግሪኩ የለም። አይሰረይለትም። 11ወደ አደባባይ#በግሪኩ ወደ ምኵራብ” ይላል። ወደ ሹሞቹና ወደ ነገሥታቱ፥ ወደ መኳንንቱም በሚወስዱአችሁ ጊዜ የምትሉትንና የምትናገሩትን አታስቡ። 12ያንጊዜ በእናንተ ላይ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ ነውና።”
ርስት ሊካፈል ስለ ወደደው ሰው
13ከሕዝቡም አንዱ፥ “መምህር ሆይ፥ ርስቴን እንዲያካፍለኝ ለወንድሜ ንገረው” አለው። 14ጌታችን ኢየሱስም፥ “አንተ ሰው፥ በእናንተ ላይ አካፋይና ዳኛ አድርጎ ማን ሾመኝ?” አለው። 15“ዕወቁ፤ ከቅሚያም ሁሉ ተጠበቁ፤ ሰው የሚድን ገንዘብ በማብዛት አይደለምና” አላቸው።
እርሻው ስለ በጀለት ባለጸጋ
16ምሳሌም መሰለላቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “እርሻው የበጀለትና ሀገር የተመቸው#“ሀገር የተመቸው” የሚለው በግሪኩ የለም። አንድ ባለጸጋ ሰው ነበረ። 17እህሌን የማኖርበት የለኝምና ምን ላድርግ ብሎ በልቡ ዐሰበ። 18እርሱም አለ፦ እንዲህ አደርጋለሁ፤ የቀድሞውን ጎተራዬን አፈርሳለሁ፤ ከእርሱ የሚበልጥ ሌላ ጎተራም እሠራለሁ፤ እህሌንና በረከቴንም በዚያ እሰበስባለሁ። 19ሰውነቴንም እንዲህ እላታለሁ፦ ሰውነቴ ሆይ፥ የሰበሰብሁልሽ ለብዙ ዓመታት የሚበቃሽ የደለበ ብዙ ሀብት አለሽ፤ እንግዲህ ወዲህ ዕረፊ፥ ብዪ፤ ጠጪም፤ ደስም ይበልሽ። 20እግዚአብሔርም፦ አንተ ሰነፍ! በዚች ሌሊት ነፍስህን ከሥጋህ ለይተው ይወስዷታል፤ እንግዲህ ያጠራቀምኸው ለማን ይሆናል? አለው። 21ሀብትን ለራሱ የሚሰበስብ፤ ሀብቱም ከእግዚአብሔር ያልሆነ እንዲሁ ነው።”
በከንቱ መጨነቅ ስለማይገባ
22ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አላቸው፥ “ስለዚህ እላችህዋለሁ፤ ለነፍሳችሁ ስለምትበሉትና ስለምትጠጡት፥ ለሰውነታችሁም ስለምትለብሱት አትጨነቁ። 23ነፍስ ከምግብ ትበልጣለችና፤ ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። 24የማይዘሩትንና የማያጭዱትን፥ ጎተራና ጕድጓድ የሌላቸውን የቍራዎችን ጫጭቶች#“ጫጭቶች” የሚለው በግሪኩ እና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ አይገኝም። ተመልከቱ፤ እግዚአብሔር ግን ይመግባቸዋል፤ እንግዲህ እናንተ ከወፎች እንዴት እጅግ አትበልጡም? 25ከእናንተስ ዐስቦ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚቻለው ማነው? 26ይህን ቀላሉን የማትችሉ ከሆነ በሌላው ለምን ትጨነቃላችሁ? 27#1ነገ. 10፥4-7፤ 2ዜ.መ. 9፥3-6። እነሆ፥ አበባዎችን እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይፈትሉም፤ አይደክሙም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞን እንኳ በክብሩ ዘመን #“ዘመን” የሚለው በግሪኩ የለም። ሁሉ ከእነርሱ እንደ አንዱ አልለበሰም። 28እነሆ፥ ዛሬ ያለውን፥ ነገም ወደ እሳት የሚጣለውን የአበባ አገዳ እግዚአብሔር እንዲህ የሚያደርገው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ ለእናንተማ እንዴት አብልጦ አያደርግላችሁ? 29እናንተም የምትበሉትንና የምትጠጡትን አትፈልጉ፤ ወዲያና ወዲህም አትበሉ፤ አትጨነቁለትም። 30ይህን ሁሉ በውጭ ያሉ የዓለም አሕዛብ ይሹታልና፤ ለእናንተስ አባታችሁ ይህን ሁሉ እንደምትሹት ያውቃል። 31ነገር ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቅ ሹ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።
32“አንተ ታናሽ መንጋ፥ አትፍራ፤ አባታችሁ መንግሥቱን ሊሰጣችሁ ወዶአልና። 33ሀብታችሁን ሸጣችሁ ምጽዋት ስጡ፤ ሌባ በማያገኝበት ነቀዝም በማያበላሽበት፥ የማያረጅ ከረጢት፥ የማያልቅም መዝገብ በሰማያት ለእናንተ አድርጉ። 34መዝገባችሁ ካለበት ልባችሁ በዚያ ይኖራልና።
ስለ መትጋት
35 #
ማቴ. 25፥1-13። “ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን። 36#ማር. 13፥34-36። እናንተም፥ በመጣና በር በመታ ጊዜ ወዲያው ይከፍቱለት ዘንድ ከሰርግ እስኪመለስ ጌታቸውን እንደሚጠብቁ ሰዎች ሁኑ። 37ጌታቸው በመጣ ጊዜ እንዲህ ሲያደርጉና ሲተጉ የሚያገኛቸው አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ወገቡን ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል፤ እየተመላለሰም ያገለግላቸዋል። 38ከሌሊቱ በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል ቢመጣና እንዲሁ ቢያገኛቸው እነዚያ አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው። 39#ማቴ. 24፥43-44። ነገር ግን ይህን ዕወቁ፤ ባለቤት ሌባ የሚመጣበትን ጊዜ ቢያውቅ ተግቶ በጠበቀ፥ ቤቱንም እንዲቈፍሩት ባልፈቀደም ነበር። 40እናንተም ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ ባልጠረጠራችሁበት ሰዓት ይመጣልና።” 41ጴጥሮስም፥ “አቤቱ፥ ይህን ምሳሌ የምትናገረው ለእኛ ነውን? ወይስ ለሁሉ ነው?” አለው። 42ጌታችንም እንዲህ አለው፥ “ምግባቸውን በየጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተሰቡ ላይ የሚሾመው ደግ#“ደግ” የሚለው በግሪኩ የለም። ታማኝና ብልህ መጋቢ ማን ይሆን? 43ጌታው በመጣ ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው አገልጋይ ብፁዕ ነው። 44እውነት እላችኋለሁ፥ በሀብቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል፤ 45ነገር ግን ያ ክፉ አገልጋይ በልቡ፦ ጌታዬ ቶሎ አይመጣም ቢል፥ በጌታው ቤት ያሉትንም ወንዶችንና ሴቶችን አገልጋዮች ሊደበድብና ሊያጕላላ ቢጀምር፥ ከሰካራሞችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ ቢሰክርም፥ 46የዚያ አገልጋይ ጌታ ባልጠረጠረው ዕለት፥ ባላወቀውም ሰዓት መጥቶ ከሁለት ይሰነጥቀዋል፤ ዕድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርገዋል። 47የጌታውን ፈቃድ ዐውቆ እንደ ፈቃዱ የማይሠራና የማያዘጋጅ የዚያ አገልጋይ ቅጣቱ ብዙ ነው። 48ያላወቀ ግን ባይሠራም ቅጣቱ ጥቂት ነው፤ ብዙ ከሰጡት ብዙ ይፈልጉበታልና። ጥቂት ከሰጡትም ጥቂት ይፈልጉበታልና።#በግሪኩ እና አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ብዙ አደራ ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል” ይላል።
ስለ ሰይፍና ስለ መለያየት
49“በምድር ላይ እሳትን አምጥቼአለሁ፤ እርስዋን ከማንደድ በቀር ምን እሻለሁ? 50#ማር. 10፥38። ነገር ግን፤ የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ፤ እስክፈጽማትም ድረስ እጅግ እታገሣለሁ።” 51ሕዝቡንም እንዲህ አላቸው፥ “ለምድር ሰላምን ያመጣሁ ይመስላችኋልን? እላችኋለሁ፤ አይደለም፤ ሰይፍንና#በግሪኩ “ሰይፍን” የሚል የለም። መለያየትን ነው እንጂ። 52ከእንግዲህስ ወዲህ አምስት ሰዎች በአንድ ቤት ቢኖሩ ሦስቱ ከሁለቱ፥ ሁለቱም ከሦስቱ ይለያሉ፤#በግሪኩ እና በብዙ የግእዝ ዘርዕ “አንዱም ከሌላው ይለያል” የሚል ይጨምራል። 53#ሚክ. 7፥6። አባት ከልጁ፥ ልጅም ከአባቱ ይለያል፤ እናት ከልጅዋ፥ ልጅም ከእናቷ ትለያለች፤ አማት ከምራቷ፥ ምራትም ከአማቷ ትለያለች።”
54ከዚህም በኋላ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፥ “ደመና በምዕራብ በኩል ደምኖ ባያችሁ ጊዜ ‘ዝናም ይመጣል’ ትላላችሁ፤ እንዲሁም ይሆናል። 55የአዜብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜም ‘ድርቅ ይሆናል፤’ ትላላችሁ እንዲሁም ይሆናል። 56እናንት ግብዞች! የሰማዩንና የምድሩን ፊት መመርመር ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እነዚህን ዘመናት መመርመርን እንዴት አታውቁም? 57እናንተ ራሳችሁ እውነቱን ለምን አትፈርዱም? 58ከባለጋራህ ጋር ወደ ሹም በምትሄድበት ጊዜ ወደ ዳኛ እንዳይወስድህ በመንገድ ሳለህ ታረቅ፤ ዕዳህንም ክፈል፤ ዳኛው ለሎሌው አሳልፎ ይሰጥሃልና። ሎሌውም በወኅኒ ቤት ያስርሃል። 59ያለብህን የመጨረሻዋን ግማሽ ሣንቲም ቢሆን እስክትጨርስ ድረስ አትወጣም እልሃለሁ።”
Nu markerat:
የሉቃስ ወንጌል 12: አማ2000
Märk
Dela
Kopiera
Vill du ha dina höjdpunkter sparade på alla dina enheter? Registrera dig eller logga in