የዮሐንስ ወንጌል 18
18
ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ስለ መስጠቱ
1ጌታችን ኢየሱስም ይህን ተናግሮ አትክልት ወደ አለበት ስፍራ ወደ ቄድሮስ ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደዚያ ገባ። 2አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም ያን ስፍራ ያውቀው ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደዚያ ብዙ ጊዜ ይሄድ ነበርና። 3ይሁዳም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን ወታደሮችን ተቀበለ፤ ሎሌዎቻቸውንም በረዳትነት ወሰደ፤ ፋኖስና የችቦ መብራት፥ የጦር መሣሪያም ይዞ ወደዚያ ሄደ። 4ጌታችን ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወደ እነርሱ ወደ ውጭ ወጣና፥ “ማንን ትሻላችሁ?” አላቸው። 5“የናዝሬቱን ኢየሱስን” ብለው መለሱለት፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ ነኝ” አላቸው፤ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም በዚያው አብሮአቸው ቆሞ ነበር። 6ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ፤ ወደ ኋላቸው ተመልሰው በምድር ላይ ወደቁ። 7ከዚህም በኋላ እንደገና፥ “ማንን ትሻላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፤ እነርሱም፥ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። 8ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ ነኝ አልኋችሁ፤ እኔን የምትሹ ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አላቸው። 9ይህም፥ “ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንድ ስንኳ አልጠፋም”#በግሪኩ “... አንዱን ስንኳ አላጠፋሁም” ይላል። ያለው ቃሉ ይፈጸም ዘንድ ነው። 10ስምዖን ጴጥሮስም ሾተል ነበረው፤ ሾተሉንም መዝዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው፤ የዚህም አገልጋይ ስም ማልኮስ ይባል ነበር። 11#ማቴ. 26፥39፤ ማር. 14፥36፤ ሉቃ. 22፥42። ጌታችን ኢየሱስም ጴጥሮስን፥ “ሾተልህን ወደ አፎቷ መልስ፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ ሳልጠጣ እተወዋለሁን?” አለው።
ወደ ሊቃነ ካህናት ስለ መሄዱ
12ጭፍሮችና የሺ አለቃው፥ የአይሁድም ሎሌዎች ጌታችን ኢየሱስን ይዘው አሰሩት። 13አስቀድሞም ወደ ሐና ወሰዱት፤ በዚያች ዓመት የካህናት አለቃ ለነበረው ለቀያፋ አማቱ ነበርና። 14#ዮሐ. 11፥49-50። ቀያፋም “ስለ ሕዝቡ ሁሉ አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል” ብሎ አይሁድን የመከራቸው ነበር።
ስለ ጴጥሮስ ክህደት
15ስምዖን ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙርም ጌታችን ኢየሱስን ከሩቅ ተከተሉት፤ ያ ደቀ መዝሙር ግን በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበር፤ ከጌታችን ኢየሱስ ጋርም ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ገባ። 16ጴጥሮስ ግን በስተውጭ በበሩ ቆሞ ነበር፤ ያም በሊቀ ካህናቱ ዘንድ ይታወቅ የነበረው ሌላው ደቀ መዝሙር ወጣና ለበረኛዪቱ ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው። 17በረኛዪቱ አገልጋይም፥ “አንተም ከዚያ ሰው ደቀ መዛሙርት ወገን አይደለህምን?” አለችው፤ እርሱም፥ “አይደለሁም” አላት። 18አገልጋዮችና ሎሌዎችም በዚያ ቆመው እሳት አንድደው ይሞቁ ነበር፤ የዚያች ሌሊት ብርድ ጽኑ ነበርና፤ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበረ።
ሊቀ ካህናቱ እንደ ጠየቀው
19ሊቀ ካህናቱም ጌታችን ኢየሱስን፦ ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። 20ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፥ “እኔ ለዓለም በግልጥ ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብም፥ በቤተ መቅደስም ሁልጊዜ አስተማርሁ፤ በስውርም የተናገርሁት አንዳች ነገር የለም። 21እንግዲህ እኔን ለምን ትጠይቀኛለህ? የተናገርሁትን የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ እኔም የተናገርሁትን እነሆ፥ እነርሱ ያውቃሉ።” 22ይህንም ባለጊዜ ከቆሙት ሎሌዎች አንዱ፥ “ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልስለታለህን?” ብሎ ጌታችን ኢየሱስን በጥፊ መታው። 23ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክርብኝ፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ለምን ትመታኛለህ?” አለው። 24ሐናም ጌታችን ኢየሱስን እንደ ታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው።
25ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር፤ “አንተስ ከእርሱ ደቀ መዛሙርት ወገን አይደለህምን?” አሉት፤ እርሱም፥ “አይደለሁም” ብሎ ካደ። 26ጴጥሮስ ጆሮውን ከቈረጠው ሰው ዘመዶች ወገን የሆነ ከሊቀ ካህናቱ አገልጋዮችም አንድ ሰው፥ “እኔ በአትክልት ቦታ ውስጥ ከእርሱ ጋር አይችህ አልነበረምን?” አለው። 27ጴጥሮስም ደግሞ ካደ፤ ያንጊዜም ዶሮ ጮኸ።
ጌታ በጲላጦስ ፊት ስለ መቆሙ
28ጌታችን ኢየሱስንም ከቀያፋ ወደ ፍርድ አደባባይ ወሰዱት፤ አይሁድ ግን ፈጽሞ ስለ ነጋ የፋሲካውን በግ ሳይበሉ እንዳይረክሱ ወደ ፍርድ አደባባይ አልገቡም። 29ጲላጦስም ወደ እነርሱ ወደ ውጭ ወጥቶ፥ “ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደሉ ምንድነው?” አላቸው። 30እነርሱም፥ “ክፉ የሠራ ባይሆንስ ወደ አንተ አሳልፈን ባልሰጠነው ነበር” ብለው መለሱለት። 31ጲላጦስም፥ “እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት” አላቸው፤ አይሁድም፥ “እኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም” አሉት። 32#ዮሐ. 3፥14፤ 12፥32። ይህም በምን ዐይነት ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት የተናገረው የጌታችን የኢየሱስ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።
33ጲላጦስም እንደገና ወደ ፍርድ አደባባይ ገብቶ ጌታችን ኢየሱስን ጠራና፥ “የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?” አለው። 34ጌታችን ኢየሱስም፥ “ይህን የምትናገር ከራስህ ነውን? ወይስ ስለ እኔ የነገረህ ሌላ አለን?” ብሎ መለሰለት። 35ጲላጦስም መልሶ፥ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ለእኔ አሳልፈው የሰጡህ ወገኖችህና ሊቃነ ካህናት አይደሉምን? Aረ ምን አድርገሃል?” አለው። 36ጌታችን ኢየሱስም፥ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ በዚህ ዓለም ብትሆን ኖሮ ለአይሁድ እንዳልሰጥ አሽከሮች በተዋጉልኝ ነበር፤ አሁንም መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” ብሎ መለሰለት። 37ጲላጦስም፥ “እንግዲያ አንተ ንጉሥ ነህን?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ራስህ ትላለህ፤ እኔ ስለዚህ ተወለድሁ፤ ስለዚህም ለእውነት ልመሰክር ወደ ዓለም መጣሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ቃሌን ይሰማኛል” አለው። 38ጲላጦስም፥ “እውነት ምንድነው?” አለው፤ ይህንም ተናግሮ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጣና እንዲህ አላቸው፥ “እኔ አንዲት ስንኳን በደል አላገኘሁበትም። 39ነገር ግን በየዓመቱ በፋሲካ በዓል ከእስረኞች አንድ እንድፈታላችሁ ልማድ አላችሁ፤ እንግዲህ የአይሁድን ንጉሥ ልፈታላችሁ ትወዳላችሁን?” አላቸው። 40ዳግመኛም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፥ “በርባንን እንጂ ይህን አይደለም፤” አሉ፤ በርባን ግን ወንበዴ ነበር።
Nu markerat:
የዮሐንስ ወንጌል 18: አማ2000
Märk
Dela
Kopiera
Vill du ha dina höjdpunkter sparade på alla dina enheter? Registrera dig eller logga in