YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘፍጥረት 8

8
የጥፋት ውሃ መጉደል
1እግዚአብሔር ኖኅንና ከእርሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ የነበሩትን አራዊትና እንስሶች ሁሉ አሰበ። ነፋስ በምድር ላይ እንዲነፍስ አደረገ፥ ውኃውም ጎደለ፥ 2ከምድር በታች ያሉት ታላቅ የውሃ መፍለቂያዎች፥ በሰማይ ያሉት የውሃ መውረጃ በሮች ሁሉ ተዘጉ፤ ዝናቡም ከሰማይ መውረዱን አቆመ። 3ውሃው ቀስ በቀስ ከምድር ላይ ቀለለ፥ ከመቶ አምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጎደለ። 4መርከቢቱም በሰባተኛው ወር፥ ከወሩም በዓሥራ ሰባተኛው ቀን በአራራት ተራሮች በአንደኛው ጫፍ ላይ ዐረፈች። 5ውኃውም እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ይጎድል ነበረ፤ በአሥረኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ጫፎች ተገለጡ።
6ከአርባ ቀንም በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ፥ 7ቁራንም ወደ ውጪ ላከው፤ እርሱም ውኃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። 8ከዚህ በኋላ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጉደሉን ለማወቅ አንዲት ርግብ ላከ። 9ነገር ግን ውሃው ገና ምድርን ሁሉ ሸፍኖ ስለ ነበር ርግቢቱ የምታርፍበት ቦታ አላገኘችም፤ ስለዚህ ኖኅ ወዳለበት መርከብ ተመልሳ መጣች፤ ኖኅም እጁን ዘርግቶ ወደ ውስጥ አስገባት። 10ሰባት ቀን ከቈየም በኋላ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት። 11ርግብም ወደ ማታ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እነሆም፥ በአፍዋ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ነበር። ኖኅም ከምድር ላይ ውኃው መጉደሉን አወቀ። 12ደግሞም ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት፤ ዳግመኛም ወደ እርሱ ሳትመለስለት ቀረች።
13የኖኅ ዕድሜ ስድስት መቶ አንድ በሆነ ጊዜ፥ በመጀመሪያው ወር፥ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን፥ ውኃው ከምድር ላይ ደረቀ፤ ኖኅ የመርከቡን ክዳን አንሥቶ ዙሪያውን ተመለከተ፤ ምድሪቱ እንደ ደረቀች አየ። 14በሁለተኛውም ወር ከወሩም በሀያ ሰባተኛው ቀን ምድር ፈጽማ ደረቀች።
ከመርከቡ ወጡ
15እግዚአብሔርም ለኖኅ እንዲህ አለው፦ 16“አንተ ከሚስትህ፥ ከልጆችህና ከልጆችህ ሚስቶች ጋር ሆነህ ከመርከቡ ውጣ፤ 17ተራብተውና ተባዝተው ምድርን ሁሉ እንዲሞሉ ከአንተ ጋር ያሉትን ሕያዋን ፍጥረቶች ሁሉ ወፎችን፥ እንስሶችንና ሌሎችን በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረቶች ሁሉ ይዘህ ውጣ።” 18ከዚህ በኋላ ኖኅ ከሚስቱ፥ ከልጆቹና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር ሆኖ ከመርከቡ ወጣ፤ 19አራዊትና እንስሶች፥ ወፎችም በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችም በየወገናቸው ሆነው ከመርከቡ ወጡ።
20ኖኅም ለጌታ መሠውያን ሠራ፤ ንጹሕ ከሆኑት እንስሶችና ወፎች ሁሉ ከየዓይነቱ አንዳንድ ወሰደ፤ መሥዋዕት እንዲሆኑም ሁሉንም በመሠዊያው ላይ አቃጠላቸው። 21የመሥዋዕቱም መዓዛ ጌታን ደስ አሰኘው፤ ጌታም በሐሳቡ እንዲህ አለ፥ “ገና ከታናሽነቱ ጊዜ ጀምሮ የሰው ሐሳብ ክፉ ነውና፥ ሰው በሚፈጽመው በደል ምክንያት ከእንግዲህ ወዲህ ምድርን አልረግምም፤ አሁን እንዳደረግሁት ሕይወት ያለውን ፍጥረት ሁሉ ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አላጠፋም። 22በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in