የሉቃስ ወንጌል 13
13
ስለ ንስሓ
1በዚያ ወራትም ሰዎች ወደ እርሱ መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስለ ቀላቀለው ስለ ገሊላ ሰዎች ነገሩት። 2ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ይህች መከራ ስለ አገኘቻቸው እነዚህ ገሊላውያን ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ተለይተው ኀጢኣተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን? 3አይደለም፤ እላችኋለሁ፤ እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደ እነርሱ ትጠፋላችሁ። 4ወይስ እነዚያ በሰሊሆም ግንብ ተጭኖ የገደላቸው ዐሥራ ስምንቱ ሰዎች ከኢየሩሳሌም ሰዎች ይልቅ ተለይተው ኀጢእታኞች ይመስሉአችኋልን? 5አይደለም፤ እላችኋለሁ፤ እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደ እነርሱ ትጠፋላችሁ።”
ፍሬ ስለሌላት በለስ
6እንዲህም ብሎ መሰለላቸው፥ “አንድ ሰው በታወቀች በወይኑ ቦታ ውስጥ#በግሪኩ “የተተከለች” ይላል። በለስ ነበረችው፤ ፍሬዋን ሊወስድ ወደ እርስዋ ሄዶ አላገኘም። 7የወይኑን ጠባቂም፦#በግሪኩ “የወይን አትክልት ሠራተኛውን” ይላል። “የዚችን በለስ ፍሬ ልወስድ ስመላለስ እነሆ፥ ሦስት ዓመት ነው፤ አላገኘሁም፤ እንግዲህስ ምድራችንን እንዳታቦዝን ቍረጣት” አለው። 8እርሱም መልሶ እንዲህ አለው፥ “አቤቱ አፈር ቈፍሬ በሥሯ እስከ አስታቅፋት፥ ፍግም እስከ አፈስባት ድረስ የዘንድሮን እንኳ ተዋት። 9ምናልባት ለከርሞ ታፈራ እንደ ሆነ፥ ያለዚያ ግን እንቈርጣታለን።”
በሰንበት ቀን ስለ ዳነችው ሴት
10በሰንበትም በአንድ ምኵራብ ውስጥ አስተማራቸው። 11ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ ጋኔን ያጐበጣት አንዲት ሴት ነበረች፤ ጐባጣም ነበረች፤ ከቶ ቀጥ ብላ መቆም አትችልም ነበር። 12ጌታችን ኢየሱስም አይቶ ራራላት፥#በግሪኩ “ራራላት” አይልም። ጠርቶም፥ “ሴትዮ፥ ከደዌሽ ተፈትተሻል” አላት። 13እጁንም በላይዋ ጫነ፤ ያንጊዜም ፈጥና ቀጥ አለች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነችው። 14#ዘፀ. 20፥9-10፤ ዘዳ. 5፥13-14። የምኵራቡ ሹምም ጌታ ኢየሱስ በሰንበት ፈውሶአልና፤ እየተቈጣ መልሶ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፥ “ሥራችሁን የምትሠሩባቸው ስድስት ቀኖች ያሉ አይደለምን? ያንጊዜ ኑና ተፈወሱ፤ በሰንበት ቀን ግን አይሆንም።” 15ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አላቸው፥ “እናንት ግብዞች፥ እናንተሳ አህያችሁን ወይም በሬአችሁን በሰንበት ቀን ገለባ ከሚበላበት አትፈቱትምን? ውኃ ልታጠጡትስ አትወስዱትምን? 16ይህቺ የአብርሃም ልጅ እነሆ፥ ሰይጣን ከአሰራት ዐሥራ ስምንት ዓመት ነው፤ እርስዋስ በሰንበት ቀን ከእስራቷ ልትፈታ አይገባምን?” 17ይህንም ባለ ጊዜ በእርሱ ላይ በጠላትነት የተነሡበት ሁሉ አፈሩ፤ ነገር ግን ሕዝቡ ሁሉ ከእርሱ ስለሚደረገው ድንቅ ነገር ሁሉ ደስ አላቸው።
ስለ ሰናፍጭ ቅንጣት ምሳሌ
18በዚያ ቀንም ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ “መንግሥተ ሰማያት#በግሪኩ “መንግሥተ እግዚአብሔር” ይላል። ምን ትመስላለች? በምንስ እመስላታለሁ? 19ሰው ወስዶ በእርሻ ውስጥ የዘራት የሰናፍጭ ቅንጣትን ትመስላለች፤ አደገች፤ ታላቅ ዛፍም ሆነች፤ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ውስጥ ተጠለሉ።”
ስለ እርሾ
20ዳግመኛም እንዲህ አለ፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እመስላታለሁ? 21ሴት ወስዳ ሦስት መስፈሪያ ዱቄት የለወሰችበትን፥ ሁሉንም እንዲቦካ ያደረገውን እርሾ ትመስላለች”።
ስለሚድኑት
22በየከተማውና በየመንደሩ እየሄደ፥ በኢየሩሳሌምም እየተመላለሰ ያስተምር ነበር። 23አንድ ሰውም፥ “አቤቱ የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን?” አለው። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ 24“ወደ ጠባቡ በር ትገቡ ዘንድ በርቱ፤ እላችኋለሁ፥ ሊገቡ የሚሹ ብዙዎች ናቸው፤ ግን አይችሉም። 25ባለቤቱ ተነሥቶ ደጁን ይዘጋልና፤ ያንጊዜ ከደጅ ቆመው፦ ‘አቤቱ፥ አቤቱ፥ ክፈትልን’ እያሉ በር ሊመቱ ይጀምራሉ፤ መልሶም፦ ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላውቃችሁም ይላቸዋል። 26ከዚህም በኋላ፦ በፊትህ በላን፥ ጠጣን፥ በአደባባያችንም አስተማርህ ልትሉ ትጀምራላችሁ። 27#መዝ. 6፥8። እርሱም እንዲህ ይላቸዋል፦ እናንተ ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላውቃችሁም፤ ዐመፅን የምታደርጉ ሁላችሁ፥ ከእኔ ራቁ፤ 28#ማቴ. 22፥13፤ 25፥30። አብርሃምን፥ ይስሐቅንና ያዕቆብን፥ ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት በአያችኋቸው ጊዜ እናንተን ወደ ውጭ ያወጡአችኋል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። 29#ማቴ. 8፥11-12። ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከደቡብ ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔርም መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ፤ 30#ማቴ. 19፥30፤ 20፥16፤ ማር. 10፥31። ኋለኞች ፊተኞች ይሆናሉ፤ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።”
ስለ ሄሮድስ
31በዚያችም ቀን ከፈሪሳውያን ወገን ሰዎች መጥተው፥ “ከዚህ ውጣና ሂድ፤ ሄሮድስ ሊገድልህ ይሻልና” አሉት። 32እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ሂዱና ያችን ቀበሮ እንዲህ በሉአት፤ እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ፤ ሕይወትንም አድላለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን እፈጽማለሁ። 33ዛሬና ነገስ አለሁ፤ በሦስተኛው ቀን ግን እሄዳለሁ፤#በግሪኩ “ዛሬና ነገ ከነገ ወዲያም እሄዳለሁ” ይላል። ነቢይ በኢየሩሳሌም እንጂ በውጭ ሊሞት አይገባውምና።
ስለ ኢየሩሳሌም መፈታት
34“ነቢያትን የምትገድሊያቸው፥ ወደ አንቺ የተላኩትን ሐዋርያትንም የምትደበድቢያቸው ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፍዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን ልሰበስባቸው ምን ያህል ወደድሁ? ነገር ግን እንቢ አላችሁ። 35#መዝ. 117፥26፤ ኤር. 22፥5። እነሆ፥ ቤታችሁ ምድረ በዳ ሆኖ ይቀርላችኋል፤ ከዛሬ ወዲያ ‘በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው’ እስክትሉ ድረስ እንደማታዩኝ እነግራችኋለሁ።”
Markert nå:
የሉቃስ ወንጌል 13: አማ2000
Marker
Del
Kopier
Vil du ha høydepunktene lagret på alle enhetene dine? Registrer deg eller logg på