ኦሪት ዘፍጥረት መግቢያ

መግቢያ
ኦሪት ዘፍጥረት ስለ ዓለማት አፈጣጠር፥ ስለ ሰው ዘር አመጣጥ፥ ስለ ኃጢአትና የሥቃይ ኑሮ አጀማመርና እግዚአብሔር ከሰው ዘር ጋር ስለ አለው ግንኙነት ይናገራል፤ ኦሪት ዘፍጥረት በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ሊመደብ ይችላል፦
1. ከምዕራፍ 1 እስከ 11 ስለ ዓለም አፈጣጠርና ስለ ሰው ዘር ቅድመ ታሪክ ይናገራል፤ የአዳምና የሔዋን፥ የቃየልና የአቤል፥ የኖኅና የጥፋት ውሃ፥ እንዲሁም የባቢሎን ግንብ ታሪክ የሚገኘው በዚህኛው ክፍል ነው።
2. ከምዕራፍ 12 እስከ 50 ይህ ክፍል ስለ እስራኤላውያን ቅድመ አባቶች ታሪክ ይናገራል፤ ከእነርሱም መካከል የመጀመሪያው በእምነቱና ለእግዚአብሔር በነበረው ታዛዥነት ታዋቂ የነበረው አብርሃም ነው፤ ከዚያም የልጁ የይስሐቅ፥ የልጁም ልጅ የነበረው የያዕቆብና የዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ታሪክ ይከተላል፤ እነዚህም ዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች፥ ዐሥራ ሁለቱን የእስራኤል ነገዶች የመሠረቱ ናቸው፤ ከእነዚህም ዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ልጆች መካከል በተለይ ዮሴፍ ላይ፥ እንዲሁም፥ ያዕቆብንና የቀሩት ልጆቹን ከነቤተሰባቸው ወደ ግብጽ ባመጣው ሁኔታ ላይ ያተኲራል።
ምንም እንኳ ይህ መጽሐፍ ስለ ሕዝቦች ታሪክ የሚናገር ቢሆን ከሁሉ በላይ የሚተርከው እግዚአብሔር ስላደረገው ሥራ ነው፤ እግዚአብሔር ዓለማትን የመፍጠሩን ታሪክ መናገር ይጀምርና እግዚአብሔር ለሕዝቡ ማሰቡን እንደማያቋርጥ የሚያመለክተውን ተስፋ በመግለጥ ይጨርሳል፤ በመጽሐፉ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ዋናው ባለ ታሪክ ስሕተት በሚፈጽሙት ላይ ፍርድና ቅጣት የሚያስተላልፈው፥ ሕዝቡን የሚመራውና የሚረዳው፥ የታሪካቸውንም ሂደት የሚያስተካክለው ራሱ እግዚአብሔር ነው። ይህ ጥንታዊ መጽሐፍ የተጻፈው የሕዝቦችን እምነት ለማስፈርና ያንንም እምነት ሕያው ሆኖ እንዲኖር ለማድረግ ነው።
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
ሀ. ፍጥረት 1፥1—2፥25
ለ. የኃጢአትና የችግር አጀማመር 3፥1-24
ሐ. ከአዳም እስከ ኖኅ 4፥1—5፥32
መ. ኖኅና የጥፋት ውሃ 6፥1—10፥32
ሠ. የባቢሎን ግንብ 11፥1-9
ረ. ከሴም እስከ አብርሃም 11፥10-32
ሰ. አባቶች አብርሃም፥ ይስሐቅ፥ ያዕቆብ 12፥1—35፥29
ሸ. የኤሳው ትውልድ 36፥1-43
ቀ. ዮሴፍና ወንድሞቹ 37፥1—45፥28
በ. እስራኤላውያን በግብጽ 46፥1—50፥26

Markering

Deel

Kopiëren

None

Wil je jouw markerkingen op al je apparaten opslaan? Meld je aan of log in