የዮሐንስ ወንጌል 8

8
በምንዝር ስለተያዘችው ሴት
1ኢየሱስ ግን ወደ ደብረዘይት ሄደ። 2ማለዳም ደግሞ ወደ መቅደስ ደረሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። ተቀምጦም ያስተምራቸው ነበር። 3ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ፤ በመካከልም እርሱዋን አቁመው 4እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ! ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች። 5#ዘሌ. 20፥10፤ ዘዳ. 22፥22-24።ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርሷ ምን ትላለህ?” 6የሚከሱበትን ምክንያት እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህንን አሉ። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤ 7#ዘዳ. 17፥7።መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ “ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወርውርባት፤” አላቸው። 8ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ። 9እነርሱም ይህን ሲሰሙ ከሽማግሌዎች ጀምሮ አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ፤ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች። 10ኢየሱስም ቀና ብሎ#8፥10 “ከሴቲቱ በቀር ማንንም ባላየ ጊዜ” የሚለውን ሐረግ የሚጨምሩ ብራናዎች አሉ። “አንቺ ሴት! ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን?” አላት። 11እርሷም “ጌታ ሆይ! አንድም እንኳን፤” አለች። ኢየሱስም “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ፤ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ፤” አላት።
ኢየሱስ የዓለም ብርሃን
12 # ጥበ. 7፥26፤ ማቴ. 5፥14፤ ዮሐ. 9፥5። ደግሞም ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ብሎ ተናገራቸው። 13#ዮሐ. 5፥31።ፈሪሳውያንም “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም፤” አሉት። 14ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ ስለ እራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድምሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንደምሄድ አታውቁም። 15እናንተ በሥጋዊ መንገድ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በአንድ ሰው ላይ እንኳ አልፈርድም። 16የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነውና፥ ብቻዬንም አይደለሁምና፥ እኔ ብፈርድ ፍርዴ እውነት ነው። 17#ዘዳ. 19፥15።የሁለት ሰዎችም ምስክርነት እውነት እንደሆነ በሕጋችሁ ትጽፎአል። 18ስለ እራሴ የምመሰክረው እኔ ነኝ፤ የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል።” 19ስለዚህም “አባትህ ወዴት ነው?” አሉት። ኢየሱስ መልሶ “እኔንም ሆነ አባቴንም አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ደግሞ ባወቃችሁ ነበር፤” አላቸው። 20ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር በግምጃ ቤት አጠገብ ይህንን ነገር ተናገረ፤ ጊዜው ገና አልደረሰምና ማንም አልያዘውም።
21ኢየሱስም ደግሞ “እኔ እሄዳለሁ፤ ትፈልጉኛላችሁም፤ በኀጢአታችሁም ትሞታላችሁ፤ እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም፤” አላቸው። 22አይሁድም “‘እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም፤’ ማለቱ እራሱን ሊገድል ይሆን?” አሉ። 23“እናንተ ከታች ናችሁ፤ እኔ ከላይ ነኝ፤እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፤ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም።” 24እንግዲህ “በኀጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤ እኔ እርሱ እንደሆንሁ ካላመናችሁ በኀጢአታችሁ ትሞታላችሁና፤” አላቸው። 25እንግዲህ “አንተ ማን ነህ?” አሉት። ኢየሱስም “ከመጀመሪያ ለእናንተ የተናገርሁት ነኝ። 26ስለ እናንተ የምናገረው የምፈርደውም ብዙ ነገር አለኝ፤ ዳሩ ግን የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔም ከእርሱ የሰማሁትን ይህን ለዓለም እናገራለሁ፤” አላቸው። 27ስለ አብ እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም። 28ስለዚህም ኢየሱስ “የሰውን ልጅ ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ እኔ እንደሆንሁ፥ እንደዚህም የምናገረው አባቴ እንዳስተማረኝ እንጂ በእራሴ ምንም እንደማላደርግ በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ። 29የላከኝም ከእኔ ጋር ነው፤ እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና፤ አብ ብቻዬን አይተወኝም፤” አላቸው። 30ይህን ሲናገር ብዙዎች በእርሱ አመኑ።
ስለ እውነት
31ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ 32#3፥14፤ 12፥32፤34።እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም አርነት ያወጣችኋል፤” 33#ማቴ. 3፥9፤ ሉቃ. 3፥8።እነርሱም መልሰው “የአብርሃም ዘር ነን፤ ከቶ ለማንም ባርያዎች አልሆንም፤ አንተ ‘አርነት ትወጣላችሁ፤’ እንዴት ትላለህ?” አሉት።
34ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው። 35ባርያም ለዘለዓለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘለዓለም ይኖራል። 36እንግዲህ ልጁ ነፃ ቢያወጣችሁ በእውነት ነፃ ትወጣላችሁ። 37የአብርሃም ዘር መሆናችሁንማ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ቃሌ በእናንተ አይኖርምና ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። 38እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ደግሞ ከአባታችሁ የሰማችሁትን ታደርጋላችሁ።”
39መልሰውም “አባታችንስ አብርሃም ነው፤” አሉት። ኢየሱስም “የአብርሃም ልጆች ብትሆኑማ ኖሮ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር። 40ነገር ግን አሁን ከእግዚአብሔር የሰማሁትን እውነት የምነገራችሁን እኔን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤ አብርሃም እንዲህ አላደረገም። 41እናንተ የአባታችሁን ሥራ ትሠራላችሁ፤” አላቸው። እነርሱም “እኛስ ከዝሙት አልተወለድንም፤ አንድ አባት አለን፤ እርሱም እግዚአብሔር ነው፤” አሉት። 42ኢየሱስም አላቸው “እግዚአብሔርስ አባታችሁ ቢሆን ኖሮ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና። 43ንግግሬን የማታስተውሉ ስለ ምንድነው? ቃሌን ልትሰሙ ስለማትችሉ ነው። 44#ጥበ. 1፥13፤ 2፥24።እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከእራሱ አፍልቆ ነው፤ ሐሰተኛ፥ የሐሰትም አባት ነውና። 45እኔ ግን እውነትን ስለምናገር አታምኑኝም። 46ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው? እውነት የምናገር ከሆንሁ እናንተ ስለምን አታምኑኝም? 47ከእግዚአብሔር የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል፤ እናንተ ከእግዚአብሔር አይደላችሁምና አትሰሙም።”
ኢየሱስና አብርሃም
48አይሁድ መልሰው “ሳምራዊ እንደሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ በመናገራችን ትክክል አይደለንምን?” አሉት። 49ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ “እኔስ ጋኔን የለብኝም፤ ነገር ግን አባቴን አከብራለሁ፤ እናንተም ታዋርዱኛላችሁ። 50እኔ ግን የእራሴን ክብር አልፈልግም፤ የሚፈልግ የሚፈርድም አለ። 51እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘለዓለም ሞትን አያይም።” 52አይሁድ “ጋኔን እንዳለብህ አሁን አወቅን። አብርሃም እንኳን ሞተ፤ ነቢያትም እንዲሁ፤ አንተ ግን ‘ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘለዓለም ሞትን አይቀምስም፤’ ትላለህ። 53በእውኑ አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? ነቢያትም ሞቱ፤ እራስህን ማን ታደርጋለህ?” አሉት። 54ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ እራሴን ባከብር ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው፤ 55ነገር ግን አላወቃችሁትም፤ እኔ ግን አውቀዋለሁ። አላውቀውም ብል ኖሮ እንደ እናንተ ሐሰተኛ በሆንሁ ነበር፤ ዳሩ ግን አውቀዋለሁ፤ ቃሉንም እጠብቃለሁ። 56አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ለማየት በመመኘት ሐሤት አደረገ፤ አየም፤ ደስም አለው።” 57አይሁድም “ገና አምሳ ዓመት አልሞላህም፤ አብርሃምን አይተሃልን?” አሉት። 58ኢየሱስም “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ፤” አላቸው። 59ስለዚህ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወረባቸው፥ ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ።

Highlight

Kongsi

Salin

None

Ingin menyimpan sorotan merentas semua peranti anda? Mendaftar atau log masuk