ኦሪት ዘፍጥረት 14
14
አብራም ሎጥን ከምርኮ እንደ መለሰው
1በሰናዖር ንጉሥ በአሚሮፌል፥ በእላሳር ንጉሥ በአርዮክ፥ በኤላም ንጉሥ በኮሎዶጎሞር፥ በአሕዛብ ንጉሥ በቴሮጋል ዘመን እንዲህ ሆነ፤ 2ከሰዶም ንጉሥ ከባላ፥ ከገሞራ ንጉሥ ከበርሳ፥ ከአዳማ ንጉሥ ከሰናአር፥ ከሲባዮ ንጉሥ ከሲምቦር፤ ሴጎር ከተባለች ከባላ ንጉሥም ጋር ጦርነት አደረጉ። 3እነዚህ ሁሉ በኤሌቄን ሸለቆ ተሰብስበው ተባበሩ፤ ይኸውም የጨው ባሕር ነው። 4ዐሥራ ሁለት ዓመት ለኮሎዶጎሞር ተገዙ፤ በዐሥራ ሦስተኛውም ዓመት ዐመፁ። 5በዐሥራ አራተኛውም ዓመት ኮሎዶጎሞርና ከእርሱ ጋር የነበሩት ነገሥታት መጡ፤ ረዐይትን በአስጣሮት ቃርናይም፥ ከእነርሱም ጋር ጽኑዓን ሰዎችንና ኦሚዎስን በሴዊ ከተማ ገደሉአቸው፤ 6በሴይር ተራራዎች ያሉ የኬሬዎስ ሰዎችንም በበረሃ አጠገብ እስከ አለችው እስከ ፋራን ዛፍ ድረስ መቱአቸው። 7ተመልሰውም ቃዴስ ወደ ተባለች ወደ ፍርድ ምንጭ መጡ፤ የአማሌቅን አለቆች ሁሉና በአሳሶን ታማር የሚኖሩ አሞራውያንንም ገደሉአቸው። 8የሰዶም ንጉሥና የገሞራ ንጉሥ፥ የአዳማ ንጉሥና የሲባዮን ንጉሥ፥ ሴጎር የተባለች የባላቅ ንጉሥም ወጡ፤ እነዚህ ሁሉ በጨው ሸለቆ በእነርሱ ላይ ለሰልፍ ወጡ፤ 9ከኤላም ንጉሥ ከኮሎዶጎሞር፥ ከአሕዛብ ንጉሥ ከቴሮጋል፥ ከሰናዖር ንጉሥ ከአሜሮፌል፥ ከእላሳር ንጉሥ ከአርዮክ ጋር ተጋጠሙ። እነዚህ አራቱ ነገሥታት ከአምስቱ ነገሥታት ጋር ተዋጉ። 10ያም የጨው ሸለቆ የዝፍት ጕድጓዶች ነበሩበት። የሰዶም ንጉሥና የገሞራ ንጉሥም ሸሹና በዚያ ወደቁ፤#ግእዙ “በዚያም ገደሉአቸው” የሚል አለው። የቀሩትም ወደ ተራራማው ሀገር ሸሹ። 11የሰዶምንና የገሞራን ፈረሶች ሁሉ፥ ስንቃቸውንም ሁሉ ይዘው ሄዱ። 12እነርሱም የአብራምን የወንድም ልጅ ሎጥንና ገንዘቡን ይዘው ሄዱ። እርሱ በሰዶም ይኖር ነበርና።
13ከአመለጡትም አንድ ሰው መጣ፤#ግእዙ በብዙ ቍጥር ይጽፋል። ለዕብራዊው ለአብራምም ነገረው፤ እርሱም የኤስኮል ወንድምና የአውናን ወንድም በሆነ በአሞራዊው የመምሬ ዛፍ ይኖር ነበር፤ እነዚያም ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን ገብተው ነበር። 14አብራምም የወንድሙ ልጅ ሎጥ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ ወገኖቹንና ቤተሰቦቹን ሁሉ ቈጠራቸው፤ እነርሱም ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ሆኑ፤ እስከ ዳን ድረስ ተከትሎ አሳደዳቸው። 15እርሱም ከብላቴኖቹ ጋር በሌሊት ደረሰባቸው፤ መታቸውም፤ በደማስቆ ግራ እስካለችውም እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። 16የሰዶምን ፈረሶች ሁሉ አስመለሰ፤ ደግሞም የወንድሙን ልጅ ሎጥንና ንብረቱን፥ ሴቶችንና ሕዝቡንም አስመለሰ።
መልከጼዴቅ አብራምን እንደ ባረከው
17ኮሎዶጎሞርንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ ከተመለሰም በኋላ የሰዶም ንጉሥ የንጉሥ ሜዳ በሆነ በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። 18የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ፤ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ። 19አብራምንም ባረከው፤ “አብራም ሰማይንና ምድርን ለፈጠረ ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፤ 20ጠላቶችህን በእጅህ የጣለልህ ልዑል እግዚአብሔርም ቡሩክ ነው” አለው። አብራምም ከሁሉ ዐሥራትን ሰጠው። 21የሰዶም ንጉሥም አብራምን፥ “ሰዎቹን ስጠኝ፤ ፈረሶቹን#ግእዙ “ጥሪትን” ይላል። ግን ለአንተ ውሰድ” አለው። 22አብራምም የሰዶምን ንጉሥ አለው፥ “ሰማይንና ምድርን ወደ ፈጠረ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጄን ከፍ አደርጋለሁ፤ 23አንተ፦ አብራምን ባለጠጋ አደረግሁት እንዳትል፥ ከአንተ ገንዘብ ሁሉ ፈትልም ቢሆን፥ የጫማ ማዘቢያም ቢሆን እንዳልወስድ፥ 24ብላቴኖች ከበሉት እህልና ከእኔ ጋር ከመጡት ድርሻ በቀር፥ አውናን፥ ኤስኮልም፥ መምሬም እነርሱ ድርሻቸውን ይውሰዱ።”
Pašlaik izvēlēts:
ኦሪት ዘፍጥረት 14: አማ2000
Izceltais
Dalīties
Kopēt
Vai vēlies, lai tevis izceltie teksti tiktu saglabāti visās tavās ierīcēs? Reģistrējieties vai pierakstieties