የሉቃስ ወንጌል 24
24
የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ
(ማቴ. 28፥1-10፤ ማር. 16፥1-8፤ ዮሐ. 20፥1-10)
1ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እጅግ ማልደው፥ ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ወደ መቃብሩ መጡ። 2ድንጋዩንም ከመቃብሩ ወዲያ ተንከባሎ አገኙት፤ 3ገብተውም የጌታን የኢየሱስን አስከሬን አላገኙም። 4እነርሱም በዚህ ሲገረሙ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ 5ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው “ሕያዉን ለምን በሙታን መካከል ትፈልጉታላችሁ? እርሱ እዚህ የለም፤ ይልቁንም ተነሥቶአል። 6#ማቴ. 16፥21፤ 17፥22፤23፤ 20፥18፤19፤ ማር. 8፥31፤ 9፥31፤ 10፥33፤34፤ ሉቃ. 9፥22፤ 18፥31-33።ገና በገሊላ እያለ የነገራችሁን አስታውሱ፥ 7የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ተላልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው።” 8እነርሱም ቃሎቹንም አስታወሱ፤ 9ከመቃብሩም ተመልሰው ይህን ሁሉ ለዐሥራ አንዱና ለሌሎች ሁሉ ነገሩአቸው። 10ይህንንም ለሐዋርያት የነገሩአቸው መግደላዊት ማርያምና ዮሐና፥ የያዕቆብም እናት ማርያም፥ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር የነበሩ ሌሎች ሴቶች ነበሩበት። 11ነገር ግን ይህ ቃል ቅዠት መስሎ ታያቸውና አላመኑአቸውም። 12ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብር ሮጠ፤ በዚያም ዝቅ ብሎ ሲመለከት ቀጭን የሐር ልብስ ለብቻ ተቀምጦ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተደነቀ ወደ ቤቱ ሄደ።
ኢየሱስ በኤማሁስ ለሁለት ደቀ መዛሙርት እንደ ተገለጠ
(ማር. 16፥12-13)
13እነሆም፥ ከእነርሱ ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ዐሥራ ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ 14ስለዚህም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። 15ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤ 16ነገር ግን እንዳያውቁት ዐይናቸው ተይዞ ነበር። 17እርሱም “አብራችሁ እየሄዳችሁ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሯቸው እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው?” አላቸው። እነርሱም አዝነው ቀጥ ብለው ቆሙ። 18ቀለዮጳ የሚባለውም አንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት “በእነዚህ ቀኖች በኢየሩሳሌም የተከሠተውን ነገር የማታውቅ እንግዳ አንተ ብቻ ነህን?” 19እርሱም “ምንድነው?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ “በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ ነው፤ 20የካህናት አለቆቻችንና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። 21እኛ ግን እስራኤልን የሚታደገው እርሱ ነው ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፤ ሆኖም ይህ ነገር ከሆነ ሦስተኛው ቀን ነው። 22ደግሞም ከእኛ ውስጥ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር። 23አስከሬኑንም ባጡ ጊዜ ‘ሕያው ነው’ የሚሉ መላእክትን በራእይ አየን ሲሉ መጥተው ነበር። 24ከእኛ ጋር ከነበሩት አንዳንዶች ወደ መቃብር ሄደው ሴቶቹ እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።” 25እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታስተውሉ፤ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ 26ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩ መግባት ይገባው የለምን?” 27ከዚህ በኋላ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን አብራራላቸው።
28ወደሚሄዱበትም መንደር ቀረቡ፤ እርሱም አልፎ የሚሄድ መሰለ። 29እነርሱ ግን “እኛ ጋር እደር፤ እየመሸ ነው፥ ቀኑም እያለቀ ነውና፤” ሲሉ አጥብቀው ለመኑት፤ እርሱም እነርሱ ጋር ሊያድር ገባ። 30ከእነርሱም ጋር በማዕድ በተቀመጠ ጊዜ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፤ ቈርሶም ሰጣቸው፤ 31ዐይናቸውም ተከፈተና አወቁት፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። 32እርስ በርሳቸውም “በመንገድ ሳለን ሲያናግረንና መጻሕፍትንም ሲያስረዳን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ። 33በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱንና ከእነርሱ ጋር የነበሩትንም በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። 34እነርሱም “ጌታ በእርግጥ ተነሥቷል፥ ለስምዖንም ታይቷል” ይሉ ነበር። 35እነርሱም በመንገድ የሆነውን፥ እንጀራውንም በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው።
ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ተገለጠ
(ማቴ. 28፥16-20፤ ማር. 16፥14-18፤ ዮሐ. 20፥19-23፤ የሐዋ. 1፥6-8)
36ይህንንም ሲነጋገሩ ሳለ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤” አላቸው። 37እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሃት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። 38እርሱም እንዲህ አላቸው “ስለምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ያድራል? 39እኔ ራሴ እንደሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ ዳስሱኝና እዩ፥ መንፈስ በእኔ እንደምታዩት፥ ሥጋና አጥንት የለውምና፤” 40ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። 41እነርሱም ከደስታ ብዛት ገና ሳያምኑ ገና በመገረም ላይ ሳሉ “በዚህ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። 42እነርሱም ትንሽ የተጠበሰ ዓሣ ሰጡት፤ 43ተቀብሎም በፊታቸው በላ።
44ከዚያም “ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግ፥ በነቢያትና በመዝሙርም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም ይገባዋል ብዬ የነገርኋችሁ ቃል ይህ ነው፤” አላቸው። 45በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ 46እንዲህም አላቸው “እንዲህ ተጽፏል፥ ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበልና፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን እንደሚነሣ፤ 47በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ እንደሚሰበክ፤ 48እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። 49#የሐዋ. 1፥4።እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በዚህች ከተማ ቆዩ።”
ኢየሱስ ወደ ሰማይ እንደ ዐረገ
(ማር. 16፥19-20፤ የሐዋ. 1፥9-11)
50 #
የሐዋ. 1፥9-11። እስከ ቢታንያም ወሰዳቸው፤ እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። 51#ሲራ. 50፥20።እየባረካቸውም ከእነርሱ ተለየ፤ ወደ ሰማይም ዐረገ። 52እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ 53ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በመቅደስ ኖሩ።
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 24: መቅካእኤ
Tya elembo
Share
Copy
Olingi kobomba makomi na yo wapi otye elembo na baapareyi na yo nyonso? Kota to mpe Komisa nkombo