ኦሪት ዘፍጥረት 4
4
ቃየልና አቤል
1አዳምም ሚስቱን ሔዋንን ዐወቃት፤ ፀነሰችም፤ ቃየልንም ወለደችው። 2እርስዋም “ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ” አለች። ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደችው። አቤልም በግ ጠባቂ ሆነ፤ ቃየልም ምድርን የሚያርስ ሆነ። 3ከብዙ ቀን በኋላም እንዲህ ሆነ፤ ቃየል ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤ 4አቤልም ደግሞ ከበጎቹ መጀመሪያ የተወለደውንና ከሰቡት አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ 5ወደ ቃየልና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየልንም እጅግ አሳዘነው፤ ፊቱም ጠቈረ። 6እግዚአብሔር አምላክም ቃየልን አለው፥ “ለምን ታዝናለህ? ለምንስ ፊትህ ጠቈረ? 7በእውነት ያመጣህልኝ አይደለም፤ አግባብስ በእውነት ታመጣልኝ ዘንድ ነበር። በደልህ፤ እንግዲህ ዝም በል፤ የወንድምህ መመለሻው ወደ አንተ ነው፤ አንተም ትሰለጥንበታለህ።” 8ቃየልም ወንድሙን አቤልን፥ “ና ወደ ሜዳ እንሂድ” አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየል በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፤ ገደለውም።
9እግዚአብሔርም#ግሪኩ “እግዚአብሔር አምላክ” ይላል። ቃየልን አለው፥ “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” ቃየልም አለ፥ “አላውቅም፤ በውኑ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?” 10እግዚአብሔርም አለው፥ “ቃየል! ምን አደረግህ? የወንድምህ የአቤል የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮሃል። 11አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ።#ግእዙ “አፍዋን የከፈተች ምድር የተረገመች ትሁን” ይላል። 12ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኀይልዋን አትሰጥህም፤ በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ።” 13ቃየልም እግዚአብሔርን አለው፥ “ኀጢአቴ ይቅር የማትባል ታላቅ ናትን? 14እነሆ፥ ዛሬ ከምድር ፊት ከአሳደድኸኝ፥ ከፊትህ እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።” 15እግዚአብሔርም አለው፥ “እንዲህ አይደለም፤ እንግዲህ ቃየልን የገደለ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልበታል።” እግዚአብሔርም ቃየልን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት።
የቃየል ትውልድ
16ቃየልም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ በኤዶም አንጻር ባለችው ኖድ በምትባለው ምድርም ኖረ። 17ቃየልም ሚስቱን ዐወቃት፤ ፀነስችም፤ ሄኖሕንም ወለደች። ከተማም ሠራ፤ የከተማይቱንም ስም በልጁ ስም “ሄኖሕ” አላት። 18ሄኖሕም ጋይዳድን#ዕብ. “ኢራድ” ይላል። ወለደ፤ ጋይዳድም ሜኤልን ወለደ፤ ሜኤልም ማቱሳኤልን ወለደ፤ ማቱሳኤልም ላሜሕን ወለደ። 19ላሜሕም ለራሱ ሁለት ሚስቶችን አገባ፤ የአንዲቱ ስም ዓዳ፥ የሁለተኛይቱ ስም ሴላ ነበር። 20ዓዳም ዮቤልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን የሚቀመጡት የዘላኖች አባት ነበረ። 21የወንድሙም ስም ኢዮቤል ነበር፤ እርሱም በገናንና መሰንቆን አስተማረ። 22ሴላም ደግሞ ቶቤልን ወለደች። እርሱም ናስና ብረትን የሚሠራ ሆነ። የእኅቱም ስም ኖሄም ነበረ። 23ላሜሕም ለሚስቶቹ ለዓዳና ለሴላ አላቸው፥ “እናንት የላሜሕ ሚስቶች ቃሌን ስሙ፤ ነገሬንም አድምጡ፤ እኔ ጐልማሳውን ስለ መቍሰሌ፤ ብላቴናውንም ስለ መወጋቴ ገድየዋለሁና፤ 24ቃየልን ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል፤ ላሜሕን ግን ሰባ ጊዜ ሰባት።”
ሴትና ሄኖስ
25አዳምም ዳግመኛ ሚስቱን ዐወቃት፤ ፀነሰችም፤ ወንድ ልጅንም ወለደች። ስሙንም ቃየል በገደለው በአቤል ፈንታ እግዚአብሔር ሌላ ዘር ተክቶልኛል ስትል ሴት አለችው። 26ሴትም ወንድ ልጅ ወለደ። ስሙንም ሄኖስ አለው፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ስም መጥራት የጀመረ ነው።#ዕብ. “በዚያን ጊዜ ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ጀመሩ” ይላል።
वर्तमान में चयनित:
ኦሪት ዘፍጥረት 4: አማ2000
हाइलाइट
शेयर
कॉपी
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in