ኦሪት ዘፍጥረት 14

14
የአራቱ ነገሥታት ዘመቻ
1በሰናዖር ንጉሥ በአምራፌል፥ በእላሳር ንጉሥ በአርዮክ፥ በኤላም ንጉሥ በኮሎዶጎምር፥ በአሕዛብ ንጉሥ በቲድዓል ዘመን እንዲህ ሆነ 2ከሰዶም ንጉሥ ከባላ፥ ከገሞራ ንጉሥ ከብርሳ፥ ከአዳማ ንጉሥ ከሰነአብ፥ ከሰቦይም ንጉሥ ከሰሜበር፥ ዞዓር ከተባለች ከቤላ ንጉሥም ጋር ሰልፍ አደረጉ። 3እነዚህ ሁሉ በሲዲም ሸለቆ ተሰብስበው ተባበሩ፥ ይኸውም የጨው ባሕር ነው። 4ዐሥራ ሁለት ዓመት ለኮሎዶጎምር ተገዝተው ነበር፥ በዓሥራ ሦስተኛውም ዓመት ዐመፁ። 5በዓሥራ አራተኛውም ዓመት ኮሎዶጎምርና ከእርሱ ጋር የነበሩት ነገሥታት መጡ፥ ራፋይምን በአስጣሮት ቃርናይም፥ ዙዚምንም በሃም፥ ኤሚምንም በሴዊ ቂርያታይም መቱ፥ 6የሖር ሰዎችንም በሴይር ተራራቸው በበረሀ አጠገብ እስካለች እስከ ኤል ፋራን ድረስ መቱ። 7ተመልሰውም ቃዴስ ወደተባለች ወደ ዓይንሚስፓጥ መጡ፥ የአማሌቅን አገር ሁሉና ደግሞ በሐሴቦን ታማር የነበረውን አሞራውያንን መቱ። 8የሰዶም ንጉሥና የገሞራ ንጉሥ፥ የአዳማ ንጉሥና የሰቦይም ንጉሥ፥ ዞዓር የተባለች የቤላ ንጉሥም ወጡ፥ እነዚህ ሁሉ በሲዲም ሸለቆ በእነርሱ ላይ ለሰልፍ ወጡ፥ 9የኤላምን ንጉሥ ኮሎዶጎምርን፥ የአሕዛብን ንጉሥ ቲድዓልን፥ የሰናዖርን ንጉሥ አምራፌልን፥ የእላሳርን ንጉሥ አርዮክን ለመውጋት አምስቱ ነገሥታት በእነዚህ በአራቱ ላይ ወጡ። 10በሲዲም ሸለቆ ግን የዝፍት ጉድጓዶች ነበሩበት። የሰዶም ንጉሥ የገሞራ ንጉሥም ሸሹና ወደዚያ ወደቁ፥ የቀሩትም ወደ ተራራ። ሸሹ። 11የሰዶምንና የገሞራን ከብት ሁሉ መብላቸውንም ሁሉ ወስደው ሄዱ። 12በሰዶም ይኖር የነበረውን የአብራምን የወንድም ልጅ ሎጥን ደግሞ ከብቱንም ወስደው ሄዱ።
13አንድ የሸሸ ሰውም መጣ፥ ለዕብራዊው ለአብራምም ነገረው፥ እርሱም የኤስኮል ወንድምና የአውናን ወንድም በሆነ በአሞራዊ መምሬ የባሉጥ ዛፎች አጠገብ ይኖር ነበር፥ እነዚያም ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን ገብተው ነበር። 14አብራምም ወንድሙ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ በቤቱ የተወለዱትን ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ብላቴኖቹን አሰለፈ፥ ፍለጋቸውንም ተከትሎ እስከ ዳን ድረስ ሄደ። 15አብራምም ጠላቶቹን ለማጥቃት አገልጋዮቹን በቡድን ከፋፍሎ በሌሊት እርሱ ከባርያዎቹ ጋር ወረደባቸው፥ መታቸውም፥ በደማስቆ ግራ እስካለችውም እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። 16ከብቱንም ሁሉ አስመለሰ፥ ደግሞም ወንድሙን ሎጥንና ከብቶቹን ሴቶችንና ሕዝቡን ደግሞ መለሰ።
መልከጼዴቅ
17ኮሎዶጎምርንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ ከተመለሰ በኋላም የሰዶም ንጉሥ የንጉሥ ሸለቆ በሆነ በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። 18#ዕብ. 7፥1-10።የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ፥ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ። 19እንዲህም ሲል ባረከውም፦
አብራም ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፥
ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ፥#14፥19 እዚህ ጋር ባረከ ማለት የእግዚአብሔርን ጸጋ፥ ትሩፋትንና መልካም ነገሮችን እንዲቀበል አደረገ ማለት ነው። ዘፍ. 9፥25፤ 27፥33፤ 48፥18፤ ባረከ የሚለው ቃል እንኳን ሰው በተናገረ ጊዜ ውጤትን ያሳያል። እግዚአብሔርም ሰዎችን ይባርካል፤ ታላቅ ታናሽን ይባርካል። ዘፍ. 1፥27፤ 12፥2፤ 28፥3-4፤ መዝ. 67፥1፤ 128፥5፤ እንደዚሁም የሰው ልጆች በፋንታቸው እግዚአብሔርን ይባርካሉ። ይህም ሲባል ስለ ታላቅነቱን እና ስለ መልካምነቱን ያመሰግናሉ፥ ውዳሴንም ያቀርባሉ ማለት ነው። ዘፍ. 24፥8፤ ዘፀ. 18፥10፤ዘዳ. 8፥10፤ 1ሳሙ. 25፥32፤ 39 እዚህ ላይ ሁለት ዓይነት ቡራኬዎች በአንድ ላይ ቀርበዋል፤ ሁለቱም ትርጉሞች በብሉይ ኪዳን ውስጥ ይታያሉ። ዘኁ. 6፥22፤ ዘዳ. 27፥14-26፤መዝ. 103፥1-2፤ 144፥1፤ ዘዳ. 2፥19-23፤ ሉቃ. 1፥68፤ 2ቀላ.፤ 1፥3፤ 1ጴጥ. 1፥3።
20ልዑል እግዚአብሔርም ይባረክ፤
ጠላቶችህን በእጅህ የጣለልህ።
አብራምም ከሁሉ አሥራትን ሰጠው። 21የሰዶም ንጉሥም አብራምን፦ ሰዎቹን ስጠኝ፥ ከብቱን ግን ለአንተ ውሰድ አለው። 22አብራምም የሰዶምን ንጉሥ አለው፦ ሰማይንና ምድርን ወደሚገዛ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጄን ከፍ አድርጌአለሁ፥ 23-24አንተ፦ አብራምን ባለ ጠጋ አደረግሁት እንዳትል፥ ብላቴኖቹ ከበሉት በቀር ከእኔ ጋር ከሄዱትም ድርሻ በቀር፥ ፈትልም ቢሆን የጫማ ማዘቢያም ቢሆን፥ ለአንተ ከሆነው ሁሉ እንዳልወስድ፥ አውናን ኤስኮልም መምሬም እነርሱ ድርሻቸውን ይውሰዱ።

Korostus

Jaa

Kopioi

None

Haluatko, että korostuksesi tallennetaan kaikille laitteillesi? Rekisteröidy tai kirjaudu sisään