YouVersion Logo
Search Icon

የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 13

13
ስለ ዘሩና ዘሪው ምሳሌ
(ማር. 4፥1-9ሉቃ. 8፥4-8)
1በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕር አጠገብ ተቀመጠ፤ 2እርሱም በታንኳ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ በወደቡ ቆመው ነበር። 3በምሳሌም ብዙ ነገራቸው እንዲህም አላቸው “እነሆ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። 4እርሱም ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። 5ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ 6ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። 7ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾህም ወጣና አነቀው። 8ሌላውም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። 9የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።”
10ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” አሉት። 11እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። 12ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 13ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ።
14‘መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፤
ማየትም ታያላችሁና አትመለከቱም።
15በዐይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥
በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥
የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና
ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዐይናቸውንም ጨፍነዋል፤’
የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል። 16የእናንተ ግን ዐይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው። 17እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፤ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም።
የዘሪው ምሳሌ ትርጕም
(ማር. 4፥13-20ሉቃ. 8፥11-15)
18“እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ። 19የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው ይመጣል፤ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። 20በጭንጫ ላይ የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ 21ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ሥር የለውም፤ በቃሉ ምክንያትም መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል። 22በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፤ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፤ የማያፈራም ይሆናል። 23በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል።”
ስለ ስንዴና እንክርዳድ ምሳሌ
24ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም አለ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች። 25ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ። 26ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ። 27የባለቤቱም ባሮች ቀርበው ‘ጌታ ሆይ! መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን? እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ?’ አሉት። 28እርሱም ‘ጠላት ይህን አደረገ፤’ አላቸው። ባሮቹም ‘እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን?’ አሉት። 29እርሱ ግን ‘እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። 30ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን “እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፤ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ፤” እላለሁ’ አለ።”
ስለ ሰናፍጭና ስለ እርሾ ምሳሌ
(ማር. 4፥30-32ሉቃ. 13፥20-21)
31ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም አለ “መንግሥተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ 32እርስዋም ከዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአታክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች።”
33ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፤ እንዲህም አለ “መንግሥተ ሰማያት ሁሉ እስኪቦካ ድረስ ሴት ወስዳ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።” 34-35ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ በነቢዩም
“በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ፤
ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ፤”
የተባለው ይፈጸም ዘንድ ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም።
የእንክርዳዱ ምሳሌ ትርጕም
36በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጕምልን፤” አሉት። 37እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው “መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ 38መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤ 39እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፤ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፤ አጫጆችም መላእክት ናቸው። 40እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። 41የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፤ 42ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። 43በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።
ስለተሰወረው መዝገብ ዕንቁና መረብ
44“ደግሞ መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ የተሰወረውን መዝገብ ትመስላለች፤ ሰውም አግኝቶ ሰወረው፤ ከደስታውም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያን እርሻ ገዛ።
45“ደግሞ መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች፤ 46ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት።
47“ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዐይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤ 48በሞላችም ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፤ ተቀምጠውም መልካሙን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አከማቹ፤ ክፉውን ግን ወደ ውጭ ጣሉት። 49በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኀጢአተኞችን ከጻድቃን መካከል ይለዩአቸዋል፤ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ 50በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”
ስለ አዲሱና ስለ አሮጌው መዝገብ
51ኢየሱስም “ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” አላቸው፤ “አዎን” አሉት። 52እርሱም “ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ደቀ መዝሙር የሆነ ጻፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል፤” አላቸው።
ኢየሱስን በናዝሬት እንደተቃወሙት
(ማር. 6፥1-6ሉቃ. 4፥16-30)
53ኢየሱስም እነዚህም ምሳሌዎች ከጨረሰ በኋላ ከዚያ ሄደ። 54ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ነበር፤ እንዲህም አሉ “ይህን ጥበብና ተአምራት ይህ ከወዴት አገኘው? 55ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ፥ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? 56እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን? እንኪያስ ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው?” ተሰናከሉበትም። 57ኢየሱስ ግን “ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤቱ በቀር ሳይከበር አይቀርም፤” አላቸው። 58በአለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in