YouVersion Logo
Search Icon

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን መግቢያ

መግቢያ
ምንም እንኳን በከፊል ቢመሳሰልም ሁለተኛው የመቃብያን መጽሐፍ ከመጀመሪያው የሚቀጥል አይደለም። የሚጀምረውም ትንሽ ቀደም ብሎ ሲሆን ከአንጥዮኩስ ኤጲፋኔስ አባት አራተኛው ሴሌኡከስ ዘመን ነው። መጽሐፉ የሚያበቃውም በይሁዳ መቃቢስ ድልና በኒቃሮን ሽንፈት ነው።
ትረካው አንጥዮኩስ ኤጲፋኔስ ሥልጣን ከጨበጠበት ከ 175 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ስምዖን እስከ ሞተበትና ዮሐንስ ሐርቃናም በ 134 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የመሪነቱን ኃላፊነት እስከተረከበ ድረስ ያለፉትን አርባ ዓመታት የዳሰሰ ነው። መጽሐፉ የእነዚያን የሩቅ ዘመናት ክስተቶች በውስጡ የያዘ በመሆኑ የላቀ ዋጋ የሚሰጠው ነው። በሕዝቡ ላይ የደረሰው መከራ የኃጢአት ውጤት ሲሆን የመሪዎቹ ድል ደግሞ በእግዚአብሔር ኃይል የተገኘ ነው።
ይህ መጽሐፍ ሰዎች ከመጥፎ ተግባራቸው እንዲመለሱ ያስተምራል። መቃቢስ ለነጻነት ያደረገው ተጋድሎ በሰማይ መላእክት የታገዘ ሲሆን በድል የተጠናቀቀውም በአምላክ ረድኤት ነው። በሕዝቡ ላይ የደረሰባቸው መሰደድ እንኳን ሳይቀር በኃጢአታቸው ብዛት የመጨረሻ ጥፋት ላይ ከመድረሳቸው በፊት ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ እግዚአብሔር ምሕረቱን ያሳየበት ድርጊት ነው። የመጽሐፉ ዓላማ የእስክንድርያዎቹ አይሁዳውያን በእስራኤል ከሚኖሩ ወንድሞቻቸው ጋር ያላቸውን አንድነት በተግባር እንዲገልጹ መቀስቀስ ነው።
ሁለተኛው መጽሐፈ መቃቢያን የቤተ መቅደሱን የማይሻር ቅድስና በማረጋገጥ፥ ቤተ መቅደሱን ባረከሰው በአሳዳጁ በአንጥዮኩስ ኤጲፋንዮስ ሞትና በቤተ መቅደሱ የምረቃ በዓል ይጀምራል። ሁለተኛው ክፍል እንደዚሁ፥ ቤተ መቅደሱን ለማጥፋት በተነሣው በአንዱ አሳዳጅ (ኒቃኖር) ሞትና በመታሰቢያ በዓል ይጀምራል።
ሁለተኛው መጽሐፈ መቃቢያን የሚከተሉትን የነገረ መለኮት ፍሬ ሐሳቦች ይዟል። አንዱ የእግዚአብሔር ሕዝብ ስለሚደርስበት መከራ ነው፤ ሌላው በመጨረሻው ቀን ስለሚሆነው የሙታን ትንሣኤ ነው፤ ሌላው ደግሞ በምድር ላይ በሚኖሩ ሰዎችና በሰማይ ባሉ ቅዱሳን መካከል የሚከናወነው የጸሎት እና የአማላጅነት ምስጢር ነው። እንዲሁም በዚህ ምድር ላይ ያሉ ለሞቱት ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የሚያቀርቡት ጸሎትንና መሥዋዕት ናቸው።
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
በግብጽ ለነበሩት አይሁድ የተላከ ደብዳቤ (1፥1—2፥18)
የፃፈው መቅድም (2፥19-32)
በሄሊዮድሮስ ቤተ መቅደሱን ለማርከስ የተደረገ ሙከራ (3፥1-40)
ርክሰትና ስደት (4፥1—7፥42)
የይሁዳ ድሎች እና የቤተ መቅደሱ መንጻት (8፥1—10፥9)
የስደቱ እንደገና መቀስቀስ (10፥10—15፥36)
የጸሐፊው መደምደሚያ (15፥37-39)
ምዕራፍ

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in