YouVersion Logo
Search Icon

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 9

9
የአንጥዮኩስ ኤጲፋኒዮስ የመጨረሻ ቀናት
1በዚሁ ጊዜ አንጥዮኩስ ከፋርስ አገር ተዋርዶ ተመለሰ። 2ዓላማው ጰርስጶሊስ ወደምትባል ከተማ ገብቶ እዚያ የሚገኘውን ምኵራብ (የአይሁድ ጸሎት ቤት) መበርበርና ከተማዋንም መያዝ ነበር፤ ሕዝቡ ግን ሮጠና የጦር መሳሪያ አነሳ፤ አንጥዮኩስ በዚያ አገር ሰዎች ተባርሮና ተዋርዶ ተመለሰ። 3ወደ ኤቅባጥን በደረሰ ጊዜ በኒቃኖርና በጢሞቶዎስ ሰዎች ላይ የደሰረባቸውን ነገር ሰማ። 4በጣም ተቆጥቶ ያበረሩትን ሰዎች በቀለ በአይሁዳውያን ላይ ለመውጣት አሰበ፤ ስለዚህ ሠረገላ ነጂውን ሰረገለውን በፍጥነት እየነዳ እንዲሄድ አዘዘው፤ ግን በእርሱ ላይ ከሰማዩ ፍርድ ወድቆበት ነበር፤ በትዕቢት ተነፍቶ፥ “በደረስሁ ጊዜ ኢየሩሳሌምን የአይሁዳውያን መቃብር አደርጋታለሁ” ሲል ተናገረ። 5ሁሉን የሚያይ እግዚአብሔር ግን የእስራኤል አምላክ በማይድንና በማይታይ በሽታ ቀሠፈው፤ ምክንያቱም ያንን ንግግሩን ተናግሮ ሲጨርስ ወዲያውኑ ብርቱ የሆድ በሽታና የመረረ የአንጀት ሠቃይ ያዘው፤ 6በሌሎች ሰዎች ሆድ ዕቃ ላይ ከባድ ሥቃይ እንዲደረስ ሁሉ ትክክለኛ ፍርድ በእርሱ ላይ ወደበቀት። 7ሆኖም ከትዕቢቱ ምንም አልታቀበም፤ ሁልጊዜ በትዕቢቱ ተሞልቶ በአይሁዳውያን ላይ በንዴት ይቃጠል ነበር፤ ጉዞውም እንዲፋጠን ያዝዝ ነበር። ከሚሮጠው ሠረገላ ክፉና ወደቀና የአካሉ መገጣጠሚያዎች ከቦታቸው ተዛነፉ፤ 8ይህ ሰው ከጥቂት ጊዜ በፊት በጭካኔ አስተሳሰቡ የባሕርን ማዕበል ማዘዝ እንኳ የሚችል መስሎ ይታየው፥ የተራሮችን ጫፍ መመዘን፥ ክብደታቸውን ለማሳወቅ የሚችል አድርጐ ራሱን ይቆጥር የነበረ፥ አሁን ግን መሬት ላይ ተጋድሞ በቃሬዛ ተሸክመው ወሰዱት። የእግዚአብሔርን ታላቅነት ሁሉም ማወቅ ቻሉ። 9ከዚህ ክፉ ሰው ሥጋ ትሎች እስኪወጡ ድረስ ገና በሕይወቱ ሳለ በበሽታና በሥቃይ እየተቆራረጠ ይወድቅ ነበር፤ የገዛ ሠራዊቱ በሙሉ በመበስበሱና በመግማቱ ያቅለሸለሻቸው ነበር። 10ይህ ከጥቂት ጊዜ በፊት የሰማይን ከዋክብት በእጁ ይነካ የመሰለው ሰው ከሰውነቱ የሚመነጨው ክርፋት የተነሣ አንስቶ ሊሸከመው የሚደፍር እንኳ ጠፋ። 11በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ በኀዘን ተሰብሮ ከታላቅ ትዕቢቱ መላቀቅና በእግዚአብሔር መቅሠፍት ውስጥ ሆኖ በሚያስጨንቅ ስቃይ ተይዞ የገዛ ራሱን ሁኔታ መገንዘብ የጀመረው። 12ከእርሱ የሚወጣውን ክርፋት እርሱ እራሱ እንኳ መታገስ (መሸከም) አቅቶት፥ “ለእግዚአብሔር መገዛት ትክክለኛ ነገር ነው፤ አንድ ሙት ሰው ከእግዚአብሔር መተካከልን እንዲተው የተገባ ነው ይል ነበር”። 13ነገር ግን ይህ ክፉ ሰው ጸሎት ቢያደርግም ጌታ ምሕረቱን አቋርጦበት ነበር፤ 14የአይሁድ መቃብር አደርጋታለሁ፥ አወድማታለሁ ብሎ በፍጥነት ወደ እርሷ ይገሰግስባት የነበረችውን ቅድስት ከተማ በነጻ እለቃታለሁ አለ፤ 15የተገባ መቃብር እንኳ እንዳያገኙና የአሞራዎች ምግብ ሆነው እንዲቀሩ፥ ልጆቻቸውም ለአውሬዎች እንዲጣሉ ብሎ የፈረደበቸውን አይሁዳውየን ከአቴና ሰዎች ጋር አስተካክላቸዋለሁ አለ፤ 16በፊት የበዘበዘውን ቤተ መቅደስ በመረጡ መባዎች አጌጠዋለሁ፤ ዕቃዎቹን አብዝቼ እመልሳለሁ፤ ለመሥዋዕት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከገዛ ራሴ ወጪ አደርጋለሁ አለ፤ 17ከዚህም በላይ አይሁዳዊ ለመሆንና የእግዚአብሐርን ኃይል እየሰበክሁ በየሀገሩ ሁሉ እዞራለሁ ሲል ተስፋ ሰጠ።
አንጥዮኩስ ለአይሁዳውያን ደብዳቤ ጻፈ
18ነገር ግን በእርሱ ላይ የአምላክ ፍርድ ወድቆበት ስለ ነበር በምንም ዓይነት ሥቃዩ ስላልተቀነሰለት በሁናቴው ተስፋ በመቁረጥ እንዲህ ሲል ለአይሁዳውያን ልመና ጻፈ፤ 19እጅግ ለተከበራችሁ አይሁዳውያን ዜጐች ከንጉሡና ከመሪው አንጥዮኩስ ሰላምና ጤና፥ ብልጽግናም ይድረሳችሁ፤ 20እናንተና ልጆቻችሁ በደኀና ከተገኛችሁ ጉዳያችሁ እንደ ሐሳባችሁ ከተፈጸመላችሁ በአምለክ ተማምነን ታላቅ ምስጋና እናቀርበለን። 21እኔ ግን ከጥቂት ጊዜ ጀምሮ ታምሜ አልጋ ላይ ነኝ፤ አክብሮታችሁና መልካም ፍቃዳችሁን አስታውሳለሁ። ከፋርስ አገር ስመለስ በአስጊ ሕመም ላይ ወድቄ ሁሉም በደህና እንዲኖሩ አስፈላጊ መሆኑን አሰብሁ። 22ግን በሁኔታዬ ተስፋ አልቆርጥም፤ ከዚህ ሕመሜ ለመዳን ብርቱ ተስፋ አለኝ፤ 23ሆኖም አባቴ በላይኞቹ ሀገሮች ላይ ጦርነት ባደረገበት ጊዜ ተተኪውን እንደወሰነ አሰብኩ፤ 24ያልታሰበ ነገር ወይም አንድ አስቸጋሪ ነገር በመጣ ጊዜ ያገሩ ሰዎች ለማን ሥልጣን እንደተሰጠ እንዲያውቁና እንዳይቸገሩ፥ 25ከእኛ አቅራቢያ ነገሥታትና የመንግሥታችን ጐረቤቶች ምቹ ጊዜ አግኝተናል ብለው እንዲያስቡና እንዳይጠብቁ ወደ ላይኛው ሀገር በፍጥነት በሄድኩበት ጊዜ ከእናንተ ለብዙዎቹ አደራ ብሎ የሰጠኋችሁን ልጄን አንጥዮኩስን ንጉሥ እንዲሆን ወስኛለሁ፤ ደብዳቤም እንዲህ ብዬ ጽፌለታለሁ፤ 26“እያንዳንዱ ግለሰብም ሆነ ለማኀበረሰቡ ያደረግሁትን ደግ ሥራ እንድታስታውሱና በእኔ ላይና በልጄ ላይ ያላችሁን መልካም አስተሳሰባችሁን ጠብቃችሁ እንድትኖሩ እለምናችኋላሁ፥ እጠይቃችኋለሁ። 27እርሱ በታዛዥነት የእኔን ሐሳብ እንደሚከተልና ከእናንተ ጋር እንደሚስማማ እርግጠኛ ነኝ”። 28በዚህ ዓይነት ይህ ነፍስ ገዳይና ስም አጥፊ ሌሎቹን ባሰቃየው መጠን አሰቃቂ ስቃይ ከተቀበለ በኋላ በሰው ሀገር አሳዛኝ ሞት ሞተ። 29ሬሳውን ወዳጁ ፊሊጶስ ወሰደው፤ ግን እርሱ በንጉሡ ልጅ በአንጥዮኩስ ስላልተማመን ወደ ግብጽ ወደ ጰጠሎሜዮስ ሄደ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in