ኦሪት ዘፍጥረት 18
18
በመምሬ የእንግዶች ክስተት
1በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የባሉጥ ዛፎች አጠገብ ተገለጠለት። 2#ዕብ. 13፥2።ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፥ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፥ ወደ ምድርም ሰገደ፥#18፥2 የአምልኮት ስግደት ሳይሆን፥ ለአክብሮት የተደረገ ማጎንበስና መደፋት ነበር። በመጀመሪያ አብርሃም እንግዶቹን እንደ ማንኛውም የሰው ልጅ ተመልክቶ በሞቀ አቀባበል ተቀብሎአቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ የሰላምታ ስግደት ለፈጣሪ ብቻ ይገባዋል የሚለው አስተምህሮ የመጣው በኋላ ነው። (ዘፍ. 2፥9፤13 እና 14 ተመ.)። እንዲህም አለ፦ 3“አቤቱ፥ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ባርያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ፥ 4ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፥ እግራችሁን ታጠቡ፥ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፥ 5ቁራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፥ ልባችሁንም ደግፋ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ፥ ስለዚህ ወደ ባርያችሁ መጥታችኋልና።” እነርሱም፦ “እንዳልህ አድርግ” አሉት። 6አብርሃምም ወደ ድንኳን ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ገባና፦ “ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፥ ለውሺውም፥ እንጎቻም አድርጊ” አላት። 7አብርሃምም ወደ ላሞቹ ሮጠ፥ እጅግ የሰባም ታናሽ ጥጃ ያዘና ለብላቴናው ሰጠው፥ ያዘጋጅም ዘንድ ተቻኰለ። 8እርጎና ወተት፥ ያዘጋጀውንም ጥጃ አመጣ፥ በፊታቸውም አቀረበው፥ እርሱም ከዛፉ በታች በፊታቸው ቆሞ ነበር፥ እነርሱም በሉ።
9እነርሱም፦ “ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?” አሉት። እርሱም፦ “በድንኳኑ ውስጥ ናት” አላቸው። 10#ሮሜ 9፥9።እርሱም፦ “የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፥ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች” አለ። ሣራም በድንኳን ደጃፍ በስተ ኋላው ሳለች ይህንን ሰማች። 11አብርሃምና ሣራም በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፥ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። 12#1ጴጥ. 3፥6።ሣራም በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች፦ “ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል።” 13እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ “ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች? 14#ሉቃ. 1፥37።በውኑ ለጌታ የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፥ ሣራም ልጅን ታገኛለች።” 15ሣራም ስለ ፈራች፦ “አልሳቅሁም” ስትል ካደች። እርሱም፦ “አይደለም፥ ሳቅሽ እንጂ” አላት።
አብርሃም ስለ ሰዶም ያቀረበው ምልጃ
16ሰዎቹም ከዚያ ተነሥተው ወደ ሰዶም አቀኑ፥ አብርሃምም ሊሸኛቸው አብሮአቸው ሄደ። 17እግዚአብሔርም አለ፦ “እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን? 18አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናልና፥ የምድር አሕዛብም ሁሉ በእርሱ ይባረካሉና። 19ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤቱን እንዲያዝዝ አውቃለሁና፥” ይህም እግዚአብሔር በአብርሃም ላይ የተናገረውን ነገር ሁሉ ያመጣ ዘንድ ነው። 20እግዚአብሔርም አለ፦ “የሰዶምና የገሞራ ጩኸት እጅግ በዝቶአልና፥ ኃጢአታቸውም እጅግ ከብዳለችና፥ 21እንግዲህስ ወደ እኔ እንደ መጣች እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደሆነ ወርጄ አያለሁ፥ እንዲሁም ባይሆን አውቃለሁ።”
22ሰዎቹም ከዚያ ፊታቸውን አቀኑ፥ ወደ ሰዶምም ሄዱ፥ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት ገና ቆሞ ነበር። 23አብርሃምም ቀረበ ዓለም፦ “በውኑ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ታጠፋለህን? 24አምሳ ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ በውኑ ሁሉን ታጠፉለህን? ከተማይቱንስ በእርሷ ስለሚገኙ አምሳ ጻድቃን አትምርምን? 25ይህ ከአንተ ይራቅ፥ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ትገድል ዘንድ፥ ጻድቁም እንደ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ እንደዚህ ያለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?” 26እግዚአብሔርም፦ “በሰዶም በከተማይቱ ውስጥ አምሳ ጻድቃን ባገኝ ስፍራውን ሁሉ ስለ እነርሱ እምራለሁ” አለ። 27አብርሃምም መለሰ ዓለም፦ “እኔ አፈርና አመድ ስሆን ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ እነሆ አንድ ጊዜ ጀመርሁ፥ 28ከአምሳው ጻድቃን አምስት ቢጐድሉ ከተማይቱን ሁሉ በአምስቱ ምክንያት ታጠፋለህን?” “ከዚያ አርባ አምስት ባገኝ አላጠፋትም” አለ። 29ደግሞም ተናገረው፥ እንዲህም አለ፦ “ምናልባት ከዚያ አርባ ቢገኙሳ?” እርሱም፦ “ለአርባው ስል አላደርገውም” አለ። 30እርሱም፦ “ጌታዬ አይቆጣ እኔም እናገራለሁ ምናልባት ከዚያ ሠላሳ ቢገኙሳ?” አለ። እርሱም፦ “ከዚያ ሰላሳ ባገኝ አላጠፋም” አለ። 31ደግሞም፦ “እነሆ፥ ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ አንድ ጊዜ ጀመርሁ፥ ምናልባት ከዚያ ሀያ ቢገኙሳ?” አለ። እርሱም፦ “ከዚያ ሀያ ቢገኙ ስለ ሀያው አላደርገውም” አለ። 32እርሱም፦ “እኔ ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ ብናገር ጌታዬ አይቆጣ፥ ምናልባት ከዚያ ዐሥር ቢገኙሳ?” አለ። እርሱም፦ “ስለ አሥሩ አላጠፋትም” አለ። 33እግዚአብሔርም ከአብርሃም ጋር ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሄደ፥ አብርሃምም ወደ ስፍራው ተመለሰ።
Zur Zeit ausgewählt:
ኦሪት ዘፍጥረት 18: መቅካእኤ
Markierung
Teilen
Kopieren
Möchtest du deine gespeicherten Markierungen auf allen deinen Geräten sehen? Erstelle ein kostenloses Konto oder melde dich an.