የሉቃስ ወንጌል 20
20
ኢየሱስ በምን ሥልጣን እንደሚሠራ የቀረበለት ጥያቄ
(ማቴ. 21፥23-27፤ ማር. 11፥27-33)
1አንድ ቀን ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ተገኝቶ ሕዝቡን ያስተምርና ወንጌልንም ያበሥር በነበረበት ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ሽማግሌዎችም ወደ እርሱ መጡ፤ 2እነርሱም “በል እስቲ ንገረን እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ወይስ እነዚህን እንድታደርግ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። 3ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ በሉ እስቲ መልሱልኝ፤ 4የዮሐንስ ጥምቀት ከእግዚአብሔር ነበረን ወይስ ከሰው?”
5እነርሱም እንዲህ እያሉ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ “ ‘ከእግዚአብሔር ነው’ ብንል፥ ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ 6‘ከሰው ነው’ ብንል ደግሞ ሕዝቡ ሁሉም በዮሐንስ ነቢይነት ስለሚያምኑ በድንጋይ ይወግሩናል።” 7ስለዚህ “ከየት እንደ ሆነ አናውቅም” ሲሉ መለሱለት። 8ኢየሱስም “እንግዲያውስ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።
የወይን አትክልት ገበሬዎች ምሳሌ
(ማቴ. 21፥33-46፤ ማር. 12፥1-12)
9ቀጥሎም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ለሕዝቡ መናገር ጀመረ፦ “አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤ ለገበሬዎች አከራየውና ወደ ሌላ አገር ሄደ፤ ሳይመለስም ብዙ ጊዜ ቈየ። #ኢሳ. 5፥1። 10ወይኑ ባፈራ ጊዜ የወይኑ ተክል ባለቤት ከፍሬው ድርሻውን እንዲቀበልለት አንድ አገልጋይ ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን አገልጋዩን ደብድበው፥ ባዶ እጁን ሰደዱት። 11እንዲሁም ሌላ አገልጋይ ቢልክ እርሱንም ደበደቡት፤ አዋርደውም ባዶ እጁን ሰደዱት፤ 12እንደገናም ሦስተኛ አገልጋይ ቢልክ እርሱንም ደብድበው አቈሰሉትና አውጥተው ጣሉት። 13ከዚህም በኋላ የወይኑ ተክል ባለቤት፦ ‘እንግዲህ ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልከዋለሁ፤ እርሱን ምናልባት ያከብሩት ይሆናል!’ አለ። 14ነገር ግን ገበሬዎቹ ባዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ ‘ይህ ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለው! ርስቱም ለእኛ ይሆናል!’ 15ስለዚህ ልጁን ከወይኑ ተክል ቦታ ወደ ውጪ አውጥተው ገደሉት። ታዲያ፥ እንግዲህ የወይኑ ተክል ጌታ በእነዚህ ገበሬዎች ላይ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? 16የወይኑ ተክል ባለቤት ራሱ ይመጣል፤ ገበሬዎቹንም ይገድላል፤ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጣል።” ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ “ይህስ ከቶ አይሁን!” አሉ።
17ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ተመልክቶ እንዲህ አለ፤
“ታዲያ፥
‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማእዘን ራስ ሆነ’ #መዝ. 118፥22።
ተብሎ የተጻፈው ምንን ያመለክታል? 18በዚያ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይሰበራል፤ ድንጋዩ በላዩ ላይ የሚወድቅበት ሰው ግን ይጨፈለቃል።”
ግብር ስለ መክፈል የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 22፥15-22፤ ማር. 12፥13-17)
19የሕግ መምህራንና የካህናት አለቆች ይህን ምሳሌ በእነርሱ ላይ እንደ ተናገረ ዐውቀው በዚያን ሰዓት ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። 20ስለዚህ ኢየሱስን ለመያዝ ምቹ ጊዜ ይጠብቁ ነበር። ለገዥው ሥልጣንና ፍርድ አሳልፈው ለመስጠት የሚያስችላቸውን የወንጀል ቃል ከእርሱ ለማግኘት ይፈልጉ ነበር፤ ስለዚህ ቅን ሰዎች መስለው፥ በንግግሩ የሚያጠምዱትን ሰላዮች ላኩበት። 21ሰላዮቹም ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ! አንተ የምትናገረውና የምታስተምረው እውነት መሆኑን እናውቃለን፤ የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት ታስተምራለህ እንጂ ለማንም አታዳላም። 22እስቲ ንገረን! በሕጋችን መሠረት ለሮም ንጉሠ ነገሥት ግብር መክፈል ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም?”
23ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ 24“እስቲ ገንዘቡን አሳዩኝ፤ በዚህ ገንዘብ ላይ የተቀረጸው መልክና የተጻፈው ስም የማን ነው?”
እነርሱም “የሮም ንጉሠ ነገሥት ነው” አሉት።
25ኢየሱስም “እንግዲያውስ የንጉሡን ለንጉሡ፥ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው።
26እነርሱም በሕዝቡ ፊት በንግግሩ ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ ስለዚህ በመልሱ ተደንቀው ዝም አሉ።
ስለ ሙታን መነሣት
(ማቴ. 22፥23-33፤ ማር. 12፥18-27)
27“ሙታን አይነሡም” የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ #ሐ.ሥ. 23፥8። 28“መምህር ሆይ! ሙሴ እንዲህ ሲል ጽፎልናል፤ ‘አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሚስቱ በሞት ቢለይ ወንድሙ ሴትዮዋን አግብቶ ለሟቹ ዘር ያትርፍለት።’ #ዘዳ. 25፥5። 29ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የሁሉም ታላቅ ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ። 30ተከታይ ወንድሙም ያቺኑ ሴት አገባት፤ 31ሦስተኛውም አገባት፤ በዚህ አኳኋን ሰባቱም አግብተዋት ልጆች ሳይወልዱ ሞቱ። 32ከሁሉም በኋላ ሴትዮዋ ሞተች። 33ሰባቱም በየተራ አግብተዋታልና ታዲያ ሙታን በሚነሡበት ጊዜ፥ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?”
34ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የዚህ ዓለም ሰዎች ያገባሉ ይጋባሉ፤ 35ከሙታን ተነሥተው በሚመጣው ዓለም ለመኖር የተገባቸው ሰዎች ግን፥ አያገቡም፤ አይጋቡም። 36እንደ መላእክት ስለሚሆኑ አይሞቱም፤ ከሞት ስለ ተነሡም የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። 37ስለ ሙታን ትንሣኤ ግን፥ ሙሴ ስለ ቊጥቋጦው እሳት በተናገረው ታሪክ ውስጥ፥ ጌታን ‘የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብ አምላክ’ ብሎ ጠርቶታል። #ዘፀ. 3፥6። 38ስለዚህ እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ ሁሉም ለእርሱ በሕይወት ይኖራሉ።”
39ከሕግ መምህራንም አንዳንዶቹ “መምህር ሆይ! መልካም ተናገርክ!” አሉ። 40ከዚያም ወዲህ ለኢየሱስ ጥያቄ ሊያቀርብለት የደፈረ ማንም የለም።
ስለ መሲሕ የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 22፥41-46፤ ማር. 12፥35-37)
41ከዚህም በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “እንዴት መሲሕን የዳዊት ልጅ ነው ይሉታል? 42-43ዳዊት እኮ ራሱ በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ፦
‘ጌታ ለጌታዬ
ጠላቶችህን በእግርህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ
በቀኜ ተቀመጥ አለው’ ይላል። #መዝ. 110፥1።
44እንግዲህ ዳዊት ራሱ ጌታ ብሎ ከጠራው ታዲያ፥ መሲሕ ለዳዊት እንዴት ልጁ ሊሆን ይችላል?”
ኢየሱስ ከሕግ መምህራን ማስጠንቀቁ
(ማቴ. 23፥1-36፤ ማር. 12፥38-40)
45ሕዝቡ ሁሉ ሲሰሙት ሳሉ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ 46“ረጃጅም ልብስ ለብሰው ወዲያና ወዲህ መዞርን፥ በገበያም የክብር ሰላምታ መቀበልን፥ በምኲራብ የክብር ወንበርን፥ በግብዣም የክብር ስፍራን ከሚወዱ ከሕግ መምህራን ተጠንቀቁ። 47እነርሱም ለታይታ በሚያቀርቡት ረጅም ጸሎት እያመካኙ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች ይበዘብዛሉ፤ ስለዚህ እነርሱን የባሰ ፍርድ ያገኛቸዋል።”
Valgt i Øjeblikket:
የሉቃስ ወንጌል 20: አማ05
Markering
Del
Kopiér
Vil du have dine markeringer gemt på tværs af alle dine enheder? Tilmeld dig eller log ind
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997