የሉቃስ ወንጌል 6
6
ስለ ሰንበት
1 #
ዘዳ. 23፥25። ከዚህም በኋላ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም እሸት ቈርጠው በእጃቸው እያሹ በሉ። 2ፈሪሳውያንም፥ “በሰንበት ሊደረግ የማይገባውን ለምን ታደርጋላችሁ?” አሉአቸው። 3#1ሳሙ. 21፥1-6። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩትም በተራቡ ጊዜ ዳዊት ያደረገውን አላነበባችሁምን? 4#ዘሌ. 24፥9። ወደ ቤተ እግዚአብሔር እንደ ገባ፥ ከካህናቱም ብቻ በቀር ሊበሉት የማይገባውን የመሥዋዕቱን ኅብስት ወስዶ እንደ በላ፥ አብረውት ለነበሩትም እንደ ሰጣቸው አላነበባችሁምን? 5የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው” አላቸው።
እጁ ስለ ደረቀችው ሰው
6ከዚህም በኋላ በሌላይቱ ሰንበት ወደ ምኵራቡ ገባና አስተማራቸው፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ። 7ጻፎችና ፈሪሳውያንም የሚከሱበት ምክንያት ያገኙ ዘንድ፥ በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ብለው ይጠባበቁት ነበር። 8እርሱ ግን ዐሳባቸውን ያውቅባቸው ነበርና እጁ የሰለለችውን ሰው፥ “ተነሥተህ በመካከል ቁም” አለው፤ ተነሥቶም ቆመ። 9ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “እጠይቃችኋለሁ፤ በሰንበት ሊደረግ የሚገባው ምንድነው? መልካም መሥራት ነውን? ወይስ ክፉ መሥራት? ነፍስን ማዳን ነውን? ወይስ መግደል?” 10እነርሱም ዝም አሉ፤ ወደ እነርሱም ዙሮ ከተመለከተ በኋላ፦ ያን ሰው፥ “እጅህን ዘርጋ” አለው፤ ሰውዬውም ዘረጋት፤ እጁም ዳነችና እንደ ሁለተኛይቱ ሆነች። 11እነርሱ ግን፥ እጅግ ተቈጡ፤ በጌታችን በኢየሱስም ምን እንድሚያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተማከሩ።
ሐዋርያትን ስለ መምረጡ
12በዚያም ወራት ጌታችን ኢየሱስ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር፤ 13ሲነጋም ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠራቸው፤ ከውስጣቸውም ዐሥራ ሁለቱን መረጠ፤ ሐዋርያት ብሎም ሰየማቸው። 14እነርሱም እነዚህ ናቸው፦ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን፥ ወንድሙም እንድርያስ፥ ያዕቆብና ዮሐንስ፥ ፊልጶስና በርተሎሜዎስ። 15ማቴዎስና ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ቀናዒ የሚባለው ስምዖን። 16የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ፥ የከዳውና#“የከዳውና” የሚለው በግሪኩ የለም። አሳልፎ የሰጠው ያስቆሮቱ ሰው ይሁዳም ናቸው። 17ከእነርሱም ጋር ወርዶ በሰፊ ቦታ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ከመላው ይሁዳና ከኢየሩሳሌም፥ ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርቻ ትምህርቱን ሊሰሙ፥ ከደዌአቸውም ሊፈወሱ የመጡት ከሕዝቡ ወገን እጅግ ብዙዎች ነበሩ። 18ክፉዎች አጋንንት ያደሩባቸውም ይፈወሱ ነበር። 19ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር፤ ኀይል ከእርሱ ይወጣ ነበርና፥ ሁሉንም ይፈውሳቸው ነበር።
በተራራ ላይ ስለ አስተማረው ትምህርት
20እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዐይኖቹን አንሥቶ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ ድሆች፥ ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና። 21ዛሬ የምትራቡ፥ ብፁዓን ናችሁ፤ ትጠግባላችሁና፤ ዛሬ የምታለቅሱ፥ ብፁዓን ናችሁ፤ ትስቃላችሁና። 22#1ጴጥ. 4፥14። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ቢጠሉአችሁ፥ ከሰው ለይተው ቢአሳድዱአችሁ፥ ቢሰድቡአችሁ፥ ክፉ ስምም ቢአወጡላችሁ ብፁዓን ናችሁ። 23#2ዜ.መ. 36፥16፤ የሐዋ. 7፥52። ያንጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ በደስታም ዝለሉ፤ ዋጋችሁ በሰማይ ብዙ ነውና፤ አባቶቻቸውም ነቢያትን እንዲሁ አድርገዋቸው ነበርና። 24ነገር ግን እናንተ ባለጠጎች፥ ወዮላችሁ፥ ደስታችሁን ጨርሳችኋልና። 25ዛሬ ለምትጠግቡ፥ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና፤ ዛሬ ለምትስቁም ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና፤ ታለቅሳላችሁምና። 26ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካሙን ነገር ቢናገሩላችሁ ወዮላችሁ፥ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲህ ያደርጉ ነበርና።
27“ለምትሰሙኝ ለእናንተ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ። 28የሚረግሙአችሁን መርቁአቸው፤ ለሚበድሉአችሁም ጸልዩላቸው። 29ጕንጭህን ለሚመታህም ሁለተኛይቱን ስጠው፤ መጐናጸፊያህን ለሚወስድም ቀሚስህን ደግሞ አትከልክለው። 30ለሚለምንህም ሁሉ ስጥ፤ ገንዘብህን የሚወስደውንም እንዲመልስ አትጠይቀው። 31#ማቴ. 7፥12። ሰዎች ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱትም እንዲሁ እናንተ አድርጉላቸው። 32የሚወድዱአችሁን ብቻ ብትወዱማ እንግዲህ ዋጋችሁ ምንድን ነው? ይህንስ ኃጥኣንም ያደርጋሉ፤ የሚወድዳቸውንም ይወድዳሉ። 33በጎ ለሚያደርጉላችሁ በጎ ብታደርጉ እንግዲህ ዋጋችሁ ምንድን ነው? እንዲህስ ኃጥኣንም ያደርጋሉ። 34እንዲከፍላችሁ ተስፋ ለምታደርጉት ብታበድሩ እንግዲህ ዋጋችሁ ምንድን ነው? ኃጥኣንም በአበደሩት ልክ ይከፍሉአቸው ዘንድ ለኃጥኣን ያበድራሉና። 35አሁንም ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካምም አድርጉላቸው፤ እንዲመልሱላችሁ ተስፋ ሳታደርጉ አበድሩ፤ ዋጋችሁም ብዙ ይሆናል፤ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለበጎዎችና#በግሪኩ “ለማያመሰግኑና” ይላል። ለክፉዎች ቸር ነውና። 36ሰማያዊ#በግሪኩ እና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ሰማያዊ” የሚለው አይገኝም። አባታችሁ የሚራራ እንደ ሆነ እናንተም የምትራሩ ሁኑ። 37አትፍረዱ፥ አይፈረድባችሁምም፤ አትበድሉ፥ አይበድሉአችሁምም፤ ይቅር በሉ፥ ይቅርም ይሉአችኋል። 38ስጡ፥ ይሰጣችኋልም፤ የሞላና የበዛ፥ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በዕቅፋችሁ ይሰጡአችኋል፤ በሰፈራችሁበትም መስፈሪያ ይሰፍሩላችኋል።”
39 #
ማቴ. 15፥14። ምሳሌም መሰለላቸውና እንዲህ አላቸው፥ “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱስ በጕድጓድ ውስጥ ይወድቁ የለምን? 40#ማቴ. 10፥24-25፤ ዮሐ. 13፥16፤ 15፥20። ከመምህሩ የሚበልጥ ደቀ መዝሙር የለም፤ ለሁሉም መጠኑ እንደ መምህሩ ይሆናል። 41በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጕድፍ ለምን ታያለህ? በዐይንህ ውስጥ ያለውን ምሰሶ አታይምን? 42ወንድምህንም፦ ወንድሜ ሆይ፥ ታገሥ፤ በዐይንህ ያለውን ጕድፍ ላውጣልህ ልትለው እንደምን ትችላለህ? አንተ ግን በዐይንህ ውስጥ ያለውን ምሰሶ አታይም፤ አንተ ግብዝ፥ አስቀድሞ ከዐይንህ ምሰሶውን አውጣ፤ ከዚህ በኋላ በባልንጀራህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጕድፍ ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ። 43ክፉ ፍሬን የሚያፈራ መልካም ዛፍ የለም፤ መልካም ፍሬ የሚያፈራ ክፉ ዛፍም የለም። 44#ማቴ. 12፥33። ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃል፤ ከእሾህ በለስን አይለቅሙም፤ ከደንደርም ወይንን አይለቅሙም። 45#ማቴ. 12፥34። መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካምን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከልቡ ክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል፤ ከልብ የተረፈውን አፍ ይናገራልና።
46“ለምን አቤቱ፥ አቤቱ፥ ትሉኛላችሁ? የምላችሁንም አታደርጉም። 47ወደ እኔ የሚመጣና ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገውም ሁሉ የሚመስለውን አሳያችኋለሁ። 48መሠረቱን አጥልቆ ቈፍሮ የመሠረተና ቤቱን በዐለት ላይ የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ብዙ ፈሳሾች በመጡ ጊዜ ጎርፎች ያን ቤት ገፉት፤ ሊያነዋውጡትም አልቻሉም፤ በዐለት ተሠርቶአልና። 49ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ግን ቤቱን ያለ መሠረት በአፈር ላይ የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ጎርፎች ገፉት፤ ወዲያውኑም ወደቀ፤ የዚያም ቤት አወዳደቁ ታላቅ ሆነ።”
Dewis Presennol:
የሉቃስ ወንጌል 6: አማ2000
Uwcholeuo
Rhanna
Copi
Eisiau i'th uchafbwyntiau gael eu cadw ar draws dy holl ddyfeisiau? Cofrestra neu mewngofnoda