Logo YouVersion
Eicon Chwilio

የሉቃስ ወንጌል 22

22
አይሁድ ኢየሱስን ለመግደል እንዳሤሩ
(ማቴ. 26፥1-5ማር. 14፥1-2ዮሐ. 11፥45-53)
1 # ዘፀ. 12፥1-27። ፋሲካም ተብሎ የሚጠራው የቂጣ በዓል ቀረበ። 2የካህናት አለቆችና ጻፎች እርሱን የሚገድሉበትን መንገድ ይፈልጉ ነበር፤ ሕዝቡን ይፈሩ ነበርና።
ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት እንደተስማማ
(ማቴ. 26፥6ማር. 14፥10-11)
3ሰይጣንም ከዐሥራ ሁለቱ መካከል አንዱ በነበረውና የአስቆሮቱ በሚባለው በይሁዳ ውስጥ ገባ፤ 4ሄዶም እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ከካህናት አለቆችና ከቤተ መቅደስ አዛዦች ጋር ተነጋገረ። 5እነርሱም ደስ አላቸው፤ ገንዘብም ሊሰጡት ተዋዋሉ። 6እሺም አለ፤ ሕዝብም ባልተገኘበት ጊዜ አሳልፎ ሊሰጣቸው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር።
የመጨረሻው የፋሲካ እራት
(ማቴ. 26፥17-25ማር. 14፥12-21ዮሐ. 13፥21-30)
7የፋሲካም በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ፤ 8ጴጥሮስንና ዮሐንስንም “ፋሲካን እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን፤” ብሎ ላካቸው። 9እነርሱም “የት እንድናዘጋጅ ትፈልጋለህ?” አሉት። 10እርሱም አላቸው “እነሆ፥ ወደ ከተማ ስትገቡ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤት ተከተሉት፤ 11ለባለቤቱም ‘መምህሩ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል የት ነው?’ ይልሃል በሉት፤ 12እርሱም በሰገነት ላይ የተነጠፈውን ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን።” 13ሄደውም እንዳላቸው አገኙና ፋሲካን አሰናዱ።
የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት
(ማቴ. 26፥26-30ማር. 14፥22-261ቆሮ. 11፥23-25)
14ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። 15እርሱም “ከመከራዬ በፊት ይህን ፋሲካ ከእናንተ ጋር ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ 16በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም እላችኋለሁና፤” አላቸው። 17ጽዋንም ተቀበሎ፥ አመስግኖም “እንካችሁ፤ ይህን በመካከላችሁ ተካፈሉት፤ 18የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም እላችኋለሁና” አለ። 19ኅብስትንም አንሥቶ፥ አመስግኖ፥ ቆረሰና እንዲህ ሲል ሰጣቸው፦ “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት”። 20#ዘፀ. 24፥8፤ ኤር. 31፥31፤ 32፥40፤ ዘካ. 9፥11።እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው። 21#መዝ. 40፥10።ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ እነሆ በማዕድ ከእኔ ጋር ናት። 22የሰው ልጅስ በተወሰነው መሠረት ይሄዳል፤ ነገር ግን አሳልፎ ለሚሰጠው ሰው ወዮለት።” 23እነርሱም ከነሱ መሀል ይህንን የሚያደርገው ማን እንደሆነ ለማወቅ እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር።
ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?
24 # ማቴ. 18፥1፤ ማር. 9፥34፤ ሉቃ. 9፥46። ደግሞም ከእነሱ መሀል ማን እንደሚበልጥ ለማወቅ ክርክር ተነሣ። 25እንዲህም አላቸው አሕዛብን ንጉሦቻቸው ይገዙአቸዋል፤ በላያቸውም ሥልጣን ያላቸው በጎ አድራጊዎች ይባላሉ። 26#ማቴ. 23፥11፤ ማር. 9፥35።#ማቴ. 20፥25-27፤ ማር. 10፥42-44።እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በእናንተ መሀል እንደ ታናሽ፥ ሥልጣን ያለውም እንደሚያገለግል ይሁን። 27#ዮሐ. 13፥12-15።ለመሆኑ ማነው ታላቅ? በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል? የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በእናንተ መሀል እንደሚያገለግል ነኝ።
28እናንተ በመከራዬ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ 29አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ ለመንግሥት እሾማችኋላሁ፤ 30#ማቴ. 19፥28።በመንግሥቴም ከእኔ ማዕድ ትበላላአችሁ፥ እንዲሁም ትጠጣላችሁ፤ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይም ለመፍረድ በዙፋኖች ላይ ትቀመጣላችሁ።
ጴጥሮስ እንደሚክደው ጌታ አስቀድሞ እንደ ተናገረ
(ማቴ. 26፥31-35ማር. 14፥27-31ዮሐ. 13፥36-38)
31ጌታም “ስምዖን ስምዖን ሆይ! እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ 32እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና፤” አለ። 33እርሱም “ጌታ ሆይ! ወደ ወኅኒም ሆነ ወደ ሞት ከአንተ ጋር ለመሄድ ዝግጁ ነኝ፤” አለው። 34እርሱ ግን “ጴጥሮስ ሆይ! ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ፥ ‘አላውቅህም’ እያልህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እልሃለሁ” አለው።
35 # ማቴ. 10፥9፤10፤ ማር. 6፥8፤9፤ ሉቃ. 9፥3፤ 10፥4። ከዚያም፥ “ያለ ቦርሳና ያለ ከረጢት፥ ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” አላቸው። እነርሱም “ምንም” አሉ። 36እርሱም “አሁን ግን ቦርሳ ያለው ይያዘው፤ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ። 37#ኢሳ. 53፥12።ይህ ‘ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ፤’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ላይ የግድ መፈጸም አለበት እላችኋልለሁ፤ አዎን፤ ስለ እኔ የተባለው አሁን ይፈጸማልና፤” አላቸው። 38እነርሱም “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ፤” አሉት። እርሱም “ይበቃል፤” አላቸው።
ኢየሱስ በደብረ ዘይት እንደ ጸለየ
(ማቴ. 26፥36-46ማር. 14፥32-42)
39እንደ ለመደው ወጥቶም ወደ ደብረዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም እንዲሁ ተከተሉት። 40ወደ ስፍራውም ደርሶ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ፤” አላቸው። 41ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፤ ተንበርክኮም፦ 42“አባት ሆይ! ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ አርቅ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን፤ የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ፤” እያለ ይጸልይ ነበር። 43ከሰማይም የሚያበረታው መልአክ ታየው። 44በስቃይ ጣር ውስጥ ሆኖ በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም ወደ መሬት እንደሚንጠባጠቡ የደም ጠብታዎች ሆኑ። 45ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጣና ከኀዘን የተነሣ ተኝተው ሲያገኛቸው 46“ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ፤” አላቸው።
ይሁዳ ኢየሱስን አሰልፎ እንደሰጠው
(ማቴ. 26፥47-56ማር. 14፥43-50ዮሐ. 18፥3-11)
47ይህንን እየተናገረ እያለ፥ እነሆ ሰዎች መጡ፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ቀረበ። 48ኢየሱስ ግን “ይሁዳ ሆይ! በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። 49በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ “ጌታ ሆይ! በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉት። 50ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው። 51ኢየሱስ ግን፦ “ይህንስ ተው” አለ፤ ጆሮውንም ዳስሶ ፈወሰው። 52ኢየሱስም ወደ እርሱ ለመጡበት ለካህናት አለቆችና ለቤተ መቅደስ አዛዦች ለሽማግሌዎችም “ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁን? 53#ሉቃ. 19፥47፤ 21፥37።ዕለት ዕለት ከእናንተ ጋር በመቅደስ ስሆን እጆቻችሁን አልዘረጋችሁብኝም፤ ሆኖም ይህ የእናንተ ጊዜና ጨለማው የሚሰፍንበት ወቅት ነው፤” አላቸው።
ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደ ካደ
(ማቴ. 26፥57-5869-75ማር. 14፥53-5466-72ዮሐ. 18፥12-1825-27)
54ይዘውም ወሰዱት፤ ወደ ሊቀ ካህናት ቤትም አስገቡት፤ ጴጥሮስም በርቀት ይከተለው ነበር። 55በግቢው መካከልም እሳት አንድደው፥ በአንድነት ተቀምጠው ሳሉ ጴጥሮስ በመካከላቸው ተቀመጠ። 56በብርሃኑም በኩል ተቀምጦ ሳለ አንዲት አገልጋይ አየችውና ትኩር ብላ “ይህም እኮ ከእርሱ ጋር ነበረ፤” አለች። 57እርሱ ግን “አንቺ ሴት! እኔ አላውቀውም፤” ሲል ካደ። 58ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላ ሰው አይቶት “አንተም እኮ ከእነርሱ አንዱ ነህ፤” አለው። ጴጥሮስ ግን “አንተ ሰው! አይደለሁም፤” አለ። 59አንድ ሰዓትም የሚያህል ቆይቶ ሌላ ሰው “እርሱ የገሊላ ሰው ነውና በእርግጥ ከእርሱ ጋር ነበረ!” ሲል አጥብቆ ተናገረ። 60ጴጥሮስ ግን “አንተ ሰው! የምትለውን አላውቅም፤” አለ። ያን ጊዜም፥ ገና እየተናገረ ሳለ ዶሮ ጮኸ። 61ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” ያለው የጌታ ቃል ትዝ አለው። 62ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።
ወታደሮች በኢየሱስ ላይ እንደ ተሳለቁበት
(ማቴ. 26፥67-68ማር. 14፥65)
63ኢየሱስንም የያዙት ሰዎች ይቀልዱበትና ይደበድቡት ነበር፤ 64ፊቱንም እየሸፈኑ “በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር፤” እያሉ ይጠይቁት ነበር። 65ሌላም ብዙ የስድብ ቃል በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር።
ኢየሱስ በፍርድ ሸንጎ ፊት እንደ ቆመ
(ማቴ. 26፥59-66ማር. 14፥55-64ዮሐ. 18፥19-24)
66ሲነጋም የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች፥ ጻፎችም ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱትና 67“አንተ መሢሕ ነህን? እስቲ ንገረን፤” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “ብነግራችሁ አታምኑም፤ 68ብጠይቅም አትመልሱልኝም፤ አትፈቱኝምም። 69ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኃይል ቀኝ ይቀመጣል።” 70ሁላቸውም “እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት። እርሱም “እኔ እንደሆንሁ እናንተ እየተናገራችሁ ነው” አላቸው። 71እነርሱም “ራሳችን ከአፉ ሰምተናልና ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል?” አሉ።

Uwcholeuo

Rhanna

Copi

None

Eisiau i'th uchafbwyntiau gael eu cadw ar draws dy holl ddyfeisiau? Cofrestra neu mewngofnoda