ইউভার্শন লোগো
সার্চ আইকন

ኦሪት ዘፍጥረት 17

17
መገረዝ የቃል ኪዳን ምልክት ስለ መሆኑ
1አብራም 99 ዓመት በሆነው ጊዜ እግዚአብሔር ተገለጠለትና “እኔ ኤልሻዳይ ሁሉን የምችል አምላክ ነኝ፤ ለእኔ በመታዘዝ ዘወትር ትክክል የሆነውን ነገር አድርግ፤ 2ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ዘርህንም እጅግ አበዛዋለሁ” አለው። 3አብራም ግንባሩ መሬት እስኪነካ ድረስ ዝቅ ብሎ ሰገደ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ 4“ከአንተ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው፤ የብዙ ሕዝቦች አባት አደርግሃለሁ፤ 5የብዙ ሕዝቦች አባት ስለማደርግህም ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ አብራም መሆኑ ቀርቶ አብርሃም ይሆናል። #17፥5 አብርሃም፦ በዕብራይስጥ “የብዙዎቹ አባት” ማለት ነው። #ሮም 4፥17። 6እጅግ ብዙ ሕዝቦች እስኪሆኑ ዘሮችህን አበዛቸዋለሁ፤ ከእነርሱም መካከል ነገሥታት የሚሆኑ ይገኛሉ።
7“በአንተና በዘርህ፥ በመጪውም ትውልድ መካከል ቃል ኪዳኔን ለዘለዓለም አጸናለሁ፤ በዚህም ዐይነት ለአንተና ከአንተ በኋላ ለሚመጣው ዘርህ አምላክ እሆናለሁ። #ሉቃ. 1፥55። 8አሁን በእንግድነት የምትኖርባትን ይህችን ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጣችኋለሁ፤ መላውን የከነዓን ምድር ለዘለዓለም እንዲወርሱት ለዘርህ እሰጣለሁ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።” #ሐ.ሥ. 7፥5።
9እንደገናም እግዚአብሔር አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “አንተና ከአንተም በኋላ የሚመጣው ዘርህ ከእኔ ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን ከትውልድ እስከ ትውልድ ጠብቁ፤ 10አንተና ከአንተ በኋላ የሚመጣው ዘርህ የምትጠብቁት ቃል ኪዳን ይህ ነው፤ በመካከላችሁ ያሉት ወንዶች ሁሉ መገረዝ አለባቸው፤ #ሐ.ሥ. 7፥8፤ ሮም 4፥11። 11ሸለፈታችሁን ትገረዛላችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል ላለው ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል፤ 12በመጪው ዘመን የሚወለድ ወንድ ልጅ ሁሉ በተወለደ በስምንተኛው ቀን ይገረዝ፤ እንዲሁም በቤትህ የተወለዱና በቤትህ ሳይወለዱ ከውጪ በገንዘብ ተገዝተው የመጡ ባሪያዎች ሳይቀሩ በዚሁ ዐይነት ይገረዙ። 13ቃል ኪዳኔ ለዘለዓለም ከእናንተ ጋር የሚኖር መሆኑን የሚያሳይ የሥጋ ምልክት እንዲሆን እያንዳንዱ ወንድ ይገረዝ። 14በሥጋው ያልተገረዘ ወንድ ሁሉ ቃል ኪዳኔን ስላላከበረ ከሕዝቡ ይወገዳል።”
15እግዚአብሔር አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ከእንግዲህ ወዲህ ሚስትህን ሣራይ ብለህ አትጥራት፤ ከዛሬ ጀምሮ የእርስዋ ስም ሣራ ነው። 16እርስዋን እባርካታለሁ፤ ከእርስዋም ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ እባርካታለሁ፤ የብዙ ሕዝቦችም እናት ትሆናለች፤ ከዘርዋም መካከል ነገሥታት የሚሆኑ ይገኛሉ።” #17፥16 ሣራ፦ በዕብራይስጥ “ልዕልት” ማለት ነው።
17አብርሃም ግንባሩ መሬት እስኪነካ ድረስ ዝቅ ብሎ ሰገደ፤ ነገር ግን “ዕድሜው መቶ ዓመት የሆነው ሰው ልጅ መውለድ ይችላልን? ሣራስ በዘጠና ዓመትዋ ልጅ ልትወልድ ትችላለችን?” ብሎ በማሰብ ሳቀ፤ 18አብርሃምም እግዚአብሔርን፦ “እስማኤልን በፊትህ ብታኖረው ምንኛ መልካም ነበር” አለው።
19እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “እንዲህስ አይሆንም፤ ነገር ግን ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ይስሐቅ ትለዋለህ፤ ቃል ኪዳኔን ከእርሱና ከዘሩ ጋር ለዘለዓለም አጸናለሁ፤ #17፥19 ይስሐቅ፦ በዕብራይስጥ “ይስቃል” ማለት ነው። 20ስለ እስማኤል ያቀረብከውንም ልመና ሰምቼአለሁ፤ እርሱንም እባርከዋለሁ፤ ብዙ ልጆችን እሰጠዋለሁ፤ ዘሩንም እጅግ አበዛዋለሁ፤ እርሱ የዐሥራ ሁለት መሳፍንት አባት ይሆናል፤ ዘሩንም ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ። 21ነገር ግን የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ ከሣራ ከሚወለደው ልጅህ ከይስሐቅ ጋር ቃል ኪዳኔን አጸናለሁ።” 22እግዚአብሔር አብርሃምን ካነጋገረው በኋላ ከእርሱ ተለይቶ ወደ ላይ ወጣ።
23እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት አብርሃም በዚያኑ ቀን ልጁን እስማኤልን ገረዘው፤ እንዲሁም በቤቱ ውስጥ የተወለዱና ከውጪ የተገዙ ባሪያዎች ሳይቀሩ፥ በቤቱ ያሉትን ወንዶች ሁሉ ገረዘ፤ 24አብርሃም ሲገረዝ ዕድሜው 99 ዓመት ነበር። 25ልጁ እስማኤል በተገረዘ ጊዜ 13 ዓመት ሆኖት ነበር፤ 26ሁለቱም የተገረዙት በአንድ ቀን ነበር። 27በቤቱ የተወለዱና ከውጪ የተገዙ ባሪያዎች ሳይቀሩ ወንዶች ሁሉ ከአብርሃም ጋር ተገረዙ።

বর্তমানে নির্বাচিত:

ኦሪት ዘፍጥረት 17: አማ05

হাইলাইট

শেয়ার

কপি

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in