YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ዘካርያስ 5

5
1ተመልሼም ዓይኖቼን አነሣሁ፥ እነሆም፥ አንድ በራሪ የመጽሐፍ ጥቅልል አየሁ። 2እርሱም፦ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም፦ በራሪ የመጽሐፍ ጥቅልል አያለሁ፥ ርዝመቱ ሀያ ክንድ ወርዱም አሥር ክንድ ነው አልሁ። 3እንዲህም አለኝ፦ ይህ በምድር ፊት ሁሉ ላይ የሚወጣው እርግማን ነው፥ የሚሰርቅ ሁሉ በእርሱ ላይ በዚህ በኩል እንደ ተጻፈው ሁሉ ይጠፋል፥ በሐሰት የሚምልም ሁሉ በእርሱ ላይ በዚያ በኩል እንደ ተጻፈው ሁሉ ይጠፋል። 4እኔ አስወጣዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ወደ ሚሰርቀውም ቤት፥ በሐሰትም በስሜ ወደሚምለው ቤት ይገባል፥ በቤቱም ውስጥ ይኖራል፥ እርሱንም፥ እንጨቱንና ድንጋዩን፥ ይበላል።
5ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ወጥቶ፦ ዓይኖችህን አንሣ፥ ይህችንም የምትወጣው ምን እንደ ሆነች እይ አለኝ። 6እኔም፦ ምንድር ናት? አልሁ። እርሱም፦ ይህች የምትወጣው የኢፍ መስፈሪያ ናት አለኝ። ደግሞም፦ በምድር ሁሉ ላይ ያለ በደላቸው ይህ ነው አለ። 7እነሆም፥ የእርሳሱን መክሊት አነሡት፥ እነሆም፥ በኢፍ መስፈሪያው ውስጥ አንዲት ሴት ተቀምጣ ነበር። 8እርሱም፦ ይህች ክፋት ናት አለኝ፥ በኢፍ መስፈሪያው ውስጥ ጣላት፥ የእርሳሱንም ጠገራ በመስፈሪያ አፍ ላይ ጣለ። 9ዓይኖቼንም አንሥቼ አየሁ፥ እነሆም፥ ሁለት ሴቶች ወጡ፥ ነፋስም በክንፎቻቸው ነበረ፥ ክንፎቻቸውም እንደ ሽመላ ክንፎች ነበሩ፥ የኢፍ መስፈሪያውንም በምድርና በሰማይ መካከል አነሡት። 10ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረውን መልአክ፦ እነዚህ የኢፍ መስፈሪያውን ወዴት ይወስዱታል? አልሁት። 11እርሱም፦ በሰናዖር ምድር ቤት ይሠሩለት ዘንድ ይወስዱታል፥ በተዘጋጀም ጊዜ በዚያ በስፍራው ይኖራል አለኝ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for ትንቢተ ዘካርያስ 5