መኃልየ መኃልይ 7
7
1አንቺ ሱላማጢስ ሆይ፥ ተመለሽ፥ ተመለሽ፥
እናይሽ ዘንድ ተመለሽ፥ ተመለሽ።
በሱላማጢስ ምን ታያላችሁ?
እርስዋ እንደ መሃናይም ዘፈን ናት።
2አንቺ የመኰንን ልጅ ሆይ፥
እግሮችሽ በጫማ ውስጥ እንዴት ውቦች ናቸው!
ዳሌዎችሽስ በአንጥረኛ እጅ እንደ ተሠሩ
እንደ ዕንቍዎች ይመስላሉ።
3እንብርትሽ የወይን ጠጅ እንደማይጐድልበት
እንደ ተነጠጠ ጽዋ ነው፥
ሆድሽ እንደ ስንዴ ክምር፥ በአበባም እንደ ታጠረ ነው።
4ሁለቱ ጡቶችሽ እንደ ሁለቱ መንታ
እንደ ሚዳቋ ግለገሎች ናቸው።
5አንገትሽ እንደ ዝሆን ጥርስ ግንብ ነው፥
ዓይኖችሽ በሐሴቦን ውስጥ በባትረቢ በር አጠገብ
እንደ ውኃ ኵሬዎች ናቸው፥
አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ አፋዛዥ እንደሚመለከት
እንደ ሊባኖስ ግንብ ነው።
6ራስሽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ በላይሽ ነው፥
የራስሽም ጠጕር እንደ ሐምራዊ ሐር ነው፥
ንጉሡ በሹርባው ታስሮአል።
7ወዳጄ ሆይ፥ እንዴት የተዋብሽ ነሽ!
እንዴትስ ደስ ታሰኛለሽ!
8ይህ ቍመትሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፥
ጡቶችሽም የወይን ዘለላ ይመስላሉ።
9ወደ ዘንባባው ዛፍ እወጣለሁ
ጫፎችዋንም እይዛለሁ አልሁ፥
ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላ
የአፍንጫሽም ሽቱ እንደ እንኮይ ናቸው።
10ጕሮሮሽ ለወዳጄ እየጣፈጠ እንደሚገባ፥
የተኙትን ከንፈሮች ይናገሩ ዘንድ እንደሚያደርግ፥
እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ነው።
11እኔ የውዴ ነኝ፥ የእርሱም ምኞት ወደ እኔ ነው።
12ውዴ ሆይ፥ ና፥ ወደ መስክ እንውጣ በመንደሮችም እንደር።
13ወደ ወይኑ ቦታ ማልደን እንሂድ፥
ወይኑ አብቦ አበባውም ፍሬ አንዠርግጎ
ሮማኑም አፍርቶ እንደ ሆነ እንይ፥
በዚያ ውዴን እሰጥሃለሁ።
14ትርንጎዎች መዓዛን ሰጡ፥
መልካሞች ፍሬዎች ሁሉ፥
አሮጌው ከአዲሱ ጋር፥ በደጃችን አሉ፥
ውዴ ሆይ፥ ሁሉን ለአንተ ጠበቅሁልህ።
Currently Selected:
መኃልየ መኃልይ 7: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in