YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘኊልቊ 10

10
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2ሁለት የብር መለከቶች አጠፍጥፈህ ለአንተ አድርግ፤ ማኅበሩን ለመጥራት ከሰፈራቸውም ለማስጓዝ ይሁኑልህ። 3ሁለቱም መለከቶች በተነፉ ጊዜ ማኅበሩ ሁሉ ወደ አንተ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይሰብሰቡ። 4አንድ መለከት ሲነፋ ታላላቆቹ የእስራኤል አእላፍ አለቆች ወደ አንተ ይሰብሰቡ። 5መለከትንም ከፍ ባለ ድምፅ ስትነፉ በምሥራቅ በኩል የሰፈሩት ይጓዙ። 6ሁለተኛውንም ከፍ ባለ ድምፅ ስትነፉ በደቡብ በኩል የሰፈሩት ይጓዙ፤ ለማስጓዝ መለከትን ይነፋሉ። 7ጉባኤውም በሚሰበሰብበት ጊዜ ንፉ፥ ነገር ግን ድምፁን ከፍ አታድርጉት። 8የአሮንም ልጆች ካህናቱ መለከቶቹን ይንፉ፤ እነርሱም ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ይሁኑ። 9በሚገፋችሁም ጠላት ላይ በምድራችሁ ወደ ሰልፍ ስትወጡ ከፍ ባለ ድምፅ መለከቶቹን ንፉ፤ በእግዚአብሔርም በአምላካችሁ ፊት ትታሰባላችሁ፥ ከጠላቶቻችሁም ትድናላችሁ። 10ደግሞ በደስታችሁ ቀን፥ በበዓላታችሁም ዘመን፥ በወርም መባቻ፥ በሚቃጠል መሥዋዕታችሁና በደኅንነት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቶቹን ንፉ፤ እነርሱም በአምላካችሁ ፊት ለመታሰቢያ ይሆኑላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 11በሁለተኛውም ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያኛው ቀን እንዲህ ሆነ፤ ደመናው ከምስክሩ ማደሪያ ላይ ተነሣ። 12የእስራኤልም ልጆች ከሲና ምድረ በዳ በየጉዞአቸው ተጓዙ፤ ደመናውም በፋራን ምድረ በዳ ቆመ። 13በመጀመሪያም እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ ተጓዙ። 14በመጀመሪያም የይሁዳ ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን አለቃ ነበረ። 15በይሳኮርም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የሶገር ልጅ ናትናኤል አለቃ ነበረ። 16በዛብሎንም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የኬሎን ልጅ ኤልያብ አለቃ ነበረ። 17ማደሪያውም ተነቀለ፤ ማደሪያውንም የተሸከሙ የጌድሶን ልጆችና የሜራሪ ልጆች ተጓዙ። 18የሮቤልም ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር አለቃ ነበረ። 19በስምዖንም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል አለቃ ነበረ። 20በጋድም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ አለቃ ነበረ። 21ቀዓታውያንም መቅደሱን ተሸክመው ተጓዙ፤ እነዚህም እስኪመጡ ድረስ እነዚያ ማደሪያውን ተከሉ። 22የኤፍሬምም ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ አለቃ ነበረ። 23በምናሴም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል አለቃ ነበረ። 24በብንያምም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን አለቃ ነበረ። 25ከሰፈሮቹ ሁሉ በኋላ የሆነ የዳን ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር አለቃ ነበረ። 26በአሴርም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የኤክራን ልጅ ፋግኤል አለቃ ነበረ። 27በንፍታሌምም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የዔናን ልጅ አኪሬ አለቃ ነበረ። 28እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ጕዞ በየሠራዊታቸው ነበረ፤ እነርሱም ተጓዙ። 29ሙሴም የሚስቱን አባት የምድያማዊውን የራጉኤልን ልጅ ኦባብን፦ እግዚአብሔር፦ ለእናንተ እሰጠዋለሁ ወዳለው ስፍራ እንሄዳለን፤ እግዚአብሔር ስለ እስራኤል መልካምን ነገር ተናግሮአልና አንተ ከእኛ ጋር ና፥ መልካምን እናደርግልሃለን አለው። 30እርሱም፦ አልሄድም፥ ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ዘመዶቼ እሄዳለሁ አለው። 31እርሱም፦ እባክህ፥ በምድረ በዳ የምንሰፍርበትን አንተ ታውቃለህና፥ እንደ ዓይኖቻችንም ትሆንልናለህና አትተወን፤ 32ከእኛም ጋር ብትሄድ እግዚአብሔር ከሚያደርግልን መልካም ነገር ሁሉ እኛ ለአንተ እናደርጋለን አለ። 33ከእግዚአብሔርም ተራራ የሦስት ቀን መንገድ ያህል ተጓዙ፤ የእግዚአብሔርም የኪዳኑ ታቦት የሚያድርበትን ስፍራ ይፈልግላቸው ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ ቀደማቸው። 34ከሰፈራቸውም በተጓዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ደመና ቀን ቀን በላያቸው ነበረ። 35ሙሴም ታቦቱ በተጓዘ ጊዜ፦ አቤቱ፥ ተነሣ፥ ጠላቶችህም ይበተኑ፥ የሚጠሉህም ከፊትህ ይሽሹ ይል ነበር። 36ባረፈም ጊዜ፦ አቤቱ፥ ወደ እስራኤል እልፍ አእላፋት ተመለስ ይል ነበር።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in