መጽሐፈ ነህምያ 2
2
ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፈቃድ እንዳገኛ
1በንጉሡ በአርጤክስስ በሀያኛው ዓመት በኒሳን ወር የወይን ጠጅ በፊቱ በነበረ ጊዜ ጠጁን አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። ቀድሞ ግን በፊቱ ያለ ኃዘን እኖር ነበር። 2ንጉሡም፦ “ሳትታመም ፊትህ ለምን አዘነ? ይህ የልብ ኅዘን ነው እንጂ ሌላ ነገር አይደለም” አለኝ። እጅግም ብዙ አድርጌ ፈራሁ። 3ንጉሡንም፦ “ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ! የአባቶቼ መቃብር ያለባት ከተማ ተፈትታለችና፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋልና ፊቴ ስለ ምን አይዘን?” አልሁት። 4ንጉሡም፦ “ምን ትለምነኛለህ?” አለኝ። እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ። 5ንጉሡንም፦ “ንጉሡን ደስ ቢያሰኝህ፥ ባሪያህም በፊትህ ሞገስ ቢያገኝ፥ እሠራው ዘንድ ወደ ይሁዳ ወደ አባቶቼ መቃብር ከተማ ስደደኝ” አልሁት። 6ንግሥቲቱም በአጠገቡ ተቀምጣ ሳለች ንጉሡ፦ “መንገድህ እስከ መቼ ድረስ ይሆናል? መቼስ ትመለሳለህ?” አለኝ። ንጉሡም ይሰድደኝ ዘንድ ደስ አለው፤ እኔም ዘመኑን ቀጠርሁለት። 7ንጉሡንም፦ “ንጉሡ ደስ ቢለው፥ እስከ ይሁዳ አገር እንዲያደርሱኝ በወንዝ ማዶ ላሉት አገረ-ገዦች ደብዳቤ ይሰጠኝ፤ 8በቤቱም አጠገብ ላለው ለግንብ በሮች፥ ለከተማውም ቅጥር፥ ለምገባበትም ቤት እንጨት እንዲሰጠኝ ለንጉሡ ዱር ጠባቂ ለአሳፍ ደብዳቤ ይሰጠኝ” አልሁት። ንጉሡም በእኔ ላይ መልካም እንደ ሆነችው እንደ አምላኬ እጅ ሰጠኝ።
9በወንዙም ማዶ ወዳሉት አለቆች መጥቼ የንጉሡን ደብዳቤ ሰጠኋቸው። ንጉሡም ከእኔ ጋር የሠራዊቱን አለቆችና ፈረሰኞች ሰደደ። 10ሖሮናዊውም ሰንባላጥና ባሪያው አሞናዊ ጦብያ ለእስራኤል ልጆች መልካምን ነገር የሚሻ ሰው እንደ መጣ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተበሳጩ።
ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ተዘዋዉሮ እንደተመለከተ
11ወደ ኢየሩሳሌምም ደረስሁ፤ በዚያም ሦስት ቀን ያህል ተቀመጥሁ። 12በሌሊትም ተነሣሁ፤ ከእኔም ጋር አያሌ ሰዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርም ለኢየሩሳሌም አደርገው ዘንድ በልቤ ያኖረውን ለማንም አላስታወቅሁም፤ ተቀምጬበት ከነበረው እንስሳ በቀር ከእኔ ጋር ምንም እንስሳ አልነበረም። 13በሸለቆውም በር ወጣሁ፤ ወደ ዘንዶውም ምንጭና ወደ ጉድፍ መጣያው በር ሄድሁ፤ የፈረሰውንም የኢየሩሳሌምን ቅጥር፥ በእሳትም የተቃጠሉትን በሮችዋን ተመለከትሁ። 14ወደ ምንጩም በርና ወደ ንጉሡ መዋኛ አለፍሁ፤ ተቀምጬበትም የነበረው እንስሳ የሚያልፍበት ስፍራ አልነበረም። 15በሌሊትም በፈፋው በኩል ወጥቼ ቅጥሩን ተመለከትሁ፤ ዘወርም ብዬ በሸለቆው በር ገባሁ፤ እንዲሁም ተመለስሁ። 16ሹማምቱ ግን ወዴት እንደ ሄድሁ፥ ምን እንዳደረግሁም አላወቁም ነበር፤ ለአይሁድና ለካህናቱ፥ ለታላላቆችና ለሹማምቱም፥ ሥራም ይሠሩ ለነበሩት ለሌሎች ገና አልተናገርሁም ነበር።
17እኔም፦ “እኛ ያለንበትን ጉስቁልና፥ ኢያሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥ በሮችዋም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ፤ አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ” አልኋቸው። 18የአምላኬም እጅ በእኔ ላይ መልካም እንደሆነች፥ ንጉሡም የነገረኝን ቃል ነገርኋቸው። እነርሱም፦ “እንነሣና እንሥራ” አሉ። እጃቸውንም ለበጎ ሥራ አበረቱ። 19ሖሮናዊውም ሰንባላጥ፥ ባሪያውም አሞናዊው ጦብያ፥ ዓረባዊዉም ጌሳም በሰሙ ጊዜ በንቀት ሳቁብን፤ ቀላል አድርገውንም፦ “ይህ የምታደርጉት ነገር ምንድር ነው? በውኑ በንጉሡ ላይ ትሸፍቱ ዘንድ ትወድዳላችሁን?” አሉ። 20እኔም መልሼ፦ “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፤ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም እድል ፈንታና መብት፥ መታሰቢያም የላችሁም አልኋቸው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነህምያ 2: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in