ኦሪት ዘሌዋውያን 11
11
1እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 2ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በሉአቸው፦ ከምድር እንስሶች ሁሉ የምትበሉአቸው እነዚህ ናቸው። 3የተሰነጠቀ ሰኮና ያለውንና የሚያመሰኳውን እንስሳ ሁሉ ብሉ። 4ነገር ግን ከሚያመሰኩት፥ ሰኮናቸውም ስንጥቅ ከሆነው ከእነዚህ አትበሉም፤ ግመል ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። 5ሽኮኮ ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። 6ጥንቸልም ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። 7እርያም ሰኮናው ተሰንጥቍል፥ ነገር ግን ስለማያመሰኳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። 8የእነዚህን ሥጋ አትበሉም፥ በድናቸውንም አትነኩም፤ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው። 9በውኃ ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ እነዚህን ትበላላችሁ፤ በውኆች በባሕሮችም በወንዞችም ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ትበላላችሁ። 10በውኆች ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ፥ በውኆች ውስጥ የሕይወት ነፍስ ካላቸው ሁሉ፥ በባሕሮችና በወንዞች ውስጥ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፉ ናቸው። 11በእናንተም ዘንድ የተጸየፉ ይሆናሉ፤ ሥጋቸውንም አትበሉም፥ በድናቸውንም ትጸየፋላችሁ። 12ክንፍና ቅርፊትም የሌላቸው በውኃ ውስጥ የሚኖሩት ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፉ ናቸው። 13ከወፎችም ወገን የምትጸየፉአቸው እነዚህ ናቸው፤ አይበሉም፤ የተጸየፉ ናቸው፤ 14ንስር፥ ገዲ፥ ዓሣ አውጭ፥ ጭላት፥ ጭልፊት 15በየወገኑ፥ ቁራ ሁሉ በየወገኑ፥ 16ሰጎን፥ ጠላቍ፥ ዝዪ፥ በቍል በየወገኑ፥ 17-18ጉጉት፥ እርኩም፥ ጋጋኖ፥ የውኃ ዶሮ፥ 19ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራ፥ ሽመላ፥ ሳቢሳ በየወገኑ፥ ጅንጁላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ። 20የሚበርርም፥ በአራት እግሮችም የሚሄድ ተንቀሳቃሽ ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፈ ነው። 21ነገር ግን ከሚበርሩት፥ አራትም እግሮች ካሉአቸው፥ ከእግሮቻቸውም በላይ በምድር ላይ የሚዘልሉባቸው ጭኖች ካሉአቸው ተንቀሳቃሾች እነዚህን ትበላላችሁ። 22ከእነርሱም እነዚህን ትበላላችሁ፤ አራቱን ዓይነት አንበጣዎች በየወገናቸው። 23ነገር ግን የሚበርር፥ አራትም እግሮች ያሉት ተንቀሳቃሽ ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፈ ነው። 24በእነዚህም ርኩስ ትሆናላችሁ፤ የእነርሱንም በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 25ከእነርሱም በድን የሚያነሣ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 26ሰኮናም ያለው፥ ነገር ግን ሰኮናው ያልተሰነጠቀ፥ የሚያመሰኳም እንሰሳ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው፤ እርሱንም የሚነካ ሁሉ ርኩስ ነው። 27በአራት እግሮቹ ከሚሄድ እንስሳ ሁሉ በመዳፎቹ ላይ የሚሄድ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው፤ የእርሱን በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 28በድናቸውንም የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። እነርሱም በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው። 29በምድር ላይም ከሚንቀሳቀስ ተንቀሳቅሳሽ እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው፤ ሙጭልጭላ፥ አይጥ፥ እንሽላሊት 30በየወገኑ፥ ኤሊ፥ አዞ፥ ገበሎ፥ አርጃኖ፥ እስስት። 31ከሚንቀሳቀሱት ሁሉ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች የሚሆኑ እነዚህ ናቸው። ከእነርሱም የሞተውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 32ከእነርሱም የሞተው በምንም ላይ ቢወድቅ እርሱ ርኩስ ነው፤ የእንጨት ዕቃ ወይም ልብስ ወይም ቁርበት ወይም ከረጢት ቢሆን የሚሠራበት ዕቃ ሁሉ እርሱ በውኃ ውስጥ ይደረግ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። 33ከእነርሱም አንዳች በውስጡ የወደቀበትን የሸክላውን ዕቃ ሁሉ ስበሩት፥ በውስጡም ያለው ሁሉ ርኩስ ነው። 34በእርሱ ውስጥ ያለው፥ ውኃም የሚፈስስበት የሚበላ መብል ሁሉ ርኩስ ነው፤ በዚህም ዕቃ ሁሉ ያለው የሚጠጣ መጠጥ ሁሉ ርኩስ ነው። 35ከእነዚህም በድን የሚወድቅበት ሁሉ ርኩስ ነው፤ እቶን ወይም ምድጃ ቢሆን ይሰባበራል፤ ርኩሶች ናቸው፤ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ይሆናሉ። 36ነገር ግን ምንጩ፥ ጕድጓዱም፥ የውኃውም ኩሬ ንጹሐን ናቸው፤ በድናቸውን ግን የሚነካ ርኩስ ነው። 37ከበድናቸውም በሚዘራ ዘር ላይ አንዳች ቢወድቅ እርሱ ንጹሕ ነው። 38ነገር ግን በዘሩ ላይ ውኃ ቢፈስስበት፥ ከዚህ በኋላ ከበድናቸው አንዳች ቢወድቅበት፥ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። 39ለመብል ከሚሆኑላችሁ እንስሶች የሞተ ቢኖር፥ በድኑን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 40ከበድኑም የሚበላ ልብሱን ያጥባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ በድኑንም የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 41በምድርም ላይ የሚንቀሳቀስ ተንቀሳቃሽ ሁሉ የተጸየፈ ነው፥ አትብሉትም። 42በሆዱ የሚሳብ፥ በአራትም እግሮች የሚሳብ፥ ብዙ እግሮችም ያሉት፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ የተጸየፉ ናቸውና አትብሉአቸው። 43በሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ ሰውነታችሁን አታስጸይፉ፤ በእነርሱም እንዳትረክሱ ሰውነታችሁን አታርክሱባቸው። 44እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና፤ ሰውነታችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ፥ እኔ ቅዱስ ነኝና፤ በምድርም ላይ በሚሳብ ተንቀሳቃሽ ሁሉ ሰውነታችሁን አታርክሱ። 45እኔ አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ እንግዲህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ። 46የእንስሳና የወፍ፥ በውኃም ውስጥ የሚንቀሳቀስ የፍጥረት ሁሉ፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀስ የፍጥረት ሁሉ ሕግ ይህ ነው። 47በርኩስና በንጹሕ መካከል፥ የሕይወት ነፍስ ካላቸውም በምትበሉትና በማትበሉት መካከል እንድትለዩ ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 11: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in