YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ኢያሱ 7

7
1የእስራኤል ልጆች ግን እርም በሆነው ነገር በደሉ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነ አካን፥ እርሱም የከርሚ ልጅ፥ የዘንበሪ ልጅ፥ የዛራ ልጅ፥ እርም ከሆነው ነገር ወሰደ፥ የእግዚአብሔርም ቁጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ።
2ኢያሱም ከቤቴል በምሥራቅ በኩል በቤትአዌን አጠገብ ወዳለችው ወደ ጋይ ሰዎችን ከኢያሪኮ ልኮ፦ ውጡ ምድሪቱንም ሰልሉ ብሎ ተናገራቸው፥ ሰዎቹም ወጡ፥ ጋይንም ሰለሉ። 3ወደ ኢያሱም ተመልሰው፦ ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጥተው ጋይን ይምቱ እንጂ ሕዝቡ ሁሉ አይውጣ፥ ጥቂቶች ናቸውና ሕዝቡ ሁሉ ወደዚያ ለመሄድ አይድከም አሉት። 4ሦስት ሺህ ያህል ሰዎችም ወደዚያ ወጡ፥ ከጋይም ሰዎች ፊት ሸሹ። 5የጋይም ሰዎች ከእነርሱ ሠላሳ ስድስት ያህል ሰዎችን መቱ፥ ከበሩ እስከ ሸባሪም ድረስ አባረሩአቸው በቁልቁለቱም መቱአቸው፥ የሕዝቡም ልብ ቀለጠ፥ እንደ ውኃም ሆነ።
6ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፥ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፉ፥ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። 7ኢያሱም አለ፦ ዋይ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ በአሞራውያን እጅ አሳልፈህ ትሰጠን ታጠፋንም ዘንድ ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገርኸው? በዮርዳኖስ ማዶ መቀመጥን በወደድን ነበር እኮ! 8ጌታ ሆይ፥ እስራኤል በጠላቶቻቸው ፊት ከሸሹ ምን እላለሁ? 9ከነዓናውያንም በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ሰምተው ይከብቡናል፥ ስማችንንም ከምድር ያጠፋሉ፥ ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድር ነው?
10እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው፦ ለምን በግምባርህ ተደፍተሃል? ቁም፥ 11እስራኤል በድሎአል፥ ያዘዝኋቸውንም ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል፥ እርም የሆነውንም ነገር ወሰዱ፥ ሰረቁም፥ ዋሹም፥ በዕቃቸውም ውስጥ ሸሸጉት። 12ስለዚህም የእስራኤል ልጆች በጠላቶቻቸው ፊት መቆም አይችሉም፥ የተረገሙ ስለ ሆኑ በጠላቶቻቸው ፊት ይሸሻሉ፥ እርም የሆነውንም ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም። 13ተነሣና ሕዝቡን ቀድስ፥ እንዲህም በላቸው፦ እስራኤል ሆይ፥ እርም የሆነ ነገር በመካከልህ አለ፥ እርምም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ እስክታጠፉ ድረስ በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም ብሎ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና እስከ ነገ ተቀደሱ። 14ነገም በየነገዳችሁ ትቀርባላችሁ፥ እግዚአብሔርም የሚለየው ነገድ በየወገኖቹ ይቀርባል፥ እግዚአብሔርም የሚለየው ወገን በየቤተ ሰቦቹ ይቀርባል፥ እግዚአብሔርም የሚለየው ቤተ ሰብ በየሰዉ ይቀርባል። 15እርም የሆነውም ነገር የተገኘበት ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን አፍርሶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ በደል አድርጎአልና እርሱና ያለው ሁሉ በእሳት ይቃጠላሉ።
16ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፥ እስራኤልንም በየነገዶቻቸው አቀረበ፥ የይሁዳም ነገድ ተለየ፥ 17የይሁዳንም ወገን አቀረበ የዛራንም ወገን ለየ፥ የዛራንም ወገን ሰዎች አቀረበ፥ 18ዘንበሪም ተለየ፥ የቤቱንም ሰዎች አቀረበ፥ ከይሁዳም ነገድ የሆነ የከርሚ ልጅ የዘንበሪ ልጅ የዛራ ልጅ አካን ተለየ። 19ኢያሱም አካንን፦ ልጄ ሆይ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብር ስጥ፥ ለእርሱም ተናዘዝ፥ ያደረግኸውንም ንገረኝ፥ አትሸሽገኝ አለው። 20አካንም መልሶ ኢያሱን፦ በእውነት የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በድያለሁ እንዲህና እንዲህም አድርጌአለሁ። 21በዘረፋ መካከል አንድ ያማረ የሰናዖር ካባ፥ ሁለት መቶም ሰቅል ብር፥ ሚዛኑም አምሳ ሰቅል የሆነ ወርቅ አይቼ ተመኘኋቸው፥ ወሰድኋቸውም፥ እነሆም፥ በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተሸሽገዋል፥ ብሩም ከሁሉ በታች ነው አለው።
22ኢያሱም መልክተኞች ሰደደ ወደ ድንኳኑም ሮጡ፥ እነሆም፥ በድንኳኑ ውስጥ ተሸሽጎ ነበር፥ ብሩም በበታቹ ነበረ። 23ከድንኳኑም ውስጥ ወስደው ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አመጡት፥ በእግዚአብሔርም ፊት አኖሩት። 24ኢያሱና እስራኤል ሁሉ የዛራን ልጅ አካንን፥ ብሩንም፥ ካባውንም፥ ወርቁንም፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹንም፥ በሬዎቹንም፥ አህያዎቹንም፥ በጎቹንም፥ ድንኳኑንም፥ ያለውንም ሁሉ ወስደው ወደ አኮር ሸለቆ አመጡአቸው። 25ኢያሱም፦ ለምን አስጨነቅኸን? እግዚአብሔር ዛሬ ያስጨንቅሃል አለው፥ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ወገሩት፥ በእሳትም አቃጠሉአቸው፥ በድንጋይም ወገሩአቸው። 26በላዩም እስከ ዛሬ ድረስ ያለ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩ፥ እግዚአብሔርም ከቁጣው ትኩሳት ተመለሰ። ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የአኮር ሸለቆ ተብሎ ተጠራ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in