መጽሐፈ ኢያሱ 5
5
1እንዲህም ሆነ፥ በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል የነበሩት የአሞራውያን ነገሥታት ሁሉ፥ በባሕሩም አጠገብ የነበሩ የከነዓናውያን ነግሥታት ሁሉ፥ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት የዮርዳኖስን ውኃ እስኪሻገሩት ድረስ እንዳደረቀ በሰሙ ጊዜ፥ ልባቸው ቀለጠ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ነፍስ ከዚያ ወዲያ አልቀረላቸውም።
2በዚያን ጊዜም እግዚአብሔር ኢያሱን፦ የባልጩት መቁረጫ ሠርተህ የእስራኤልን ልጆች ሁለተኛ ጊዜ ግረዛቸው አለው። 3ኢያሱም የባልጩት መቁረጫ ሠርቶ የግርዛት ኮረብታ በተባለ ስፍራ የእስራኤልን ልጆች ገረዘ። 4ኢያሱ የገረዘበትም ምክንያት ይህ ነው፥ ከግብፅ የወጡት ሕዝብ ወንዶች ሰልፈኞች ሁሉ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በመንገድ ላይ በምድረ በዳ ሞቱ። 5የወጡት ሕዝብ ሁሉ ተገርዘው ነበር፥ ነገር ግን ከግብፅ በወጡበት መንገድ በምድረ በዳ የተወለዱት ሕዝብ ሁሉ አልተገረዙም ነበር። 6እግዚአብሔርም ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ለእኛ ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር እንዳያሳያቸው የማለላቸው፥ ከግብፅ የወጡ የእግዚአብሔርንም ቃል ያልሰሙ፥ እነዚያ ሰልፈኞች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ የእስራኤል ልጆች አርባ ዓመት በምድረ በዳ ይሄዱ ነበር። 7ልጆቻቸውን በእነርሱ ፋንታ አስነሣ፥ እነዚህንም ኢያሱ ገረዛቸው፥ በመንገድ ሳሉ ስላልገረዙአቸው ሸለፈታሞች ነበሩና። 8ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው በተገረዙ ጊዜ እስኪድኑ ድረስ በሰፈር ውስጥ በየስፍራቸው ተቀመጡ። 9እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ አለው፥ ስለዚህ የዚያን ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ጌልገላ ተብሎ ተጠራ።
10የእስራኤልም ልጆች በጌልገላ ሰፈሩ፥ ከወሩም በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በኢያሪኮ ሜዳ ፋሲካ አደረጉ። 11ከፋሲካውም በኋላ በነጋው የምድሪቱን ፍሬ የቂጣ እንጎቻ ቆሎም በዚያው ቀን በሉ። 12በነጋውም ከምድሪቱ ፍሬ ከበሉ በኋላ መናው ቀረ፥ ከዚያም በኋላ ለእስራኤል ልጆች መና አልመጣላቸውም፥ ነገር ግን በዚያው ዓመት የከነዓንን ምድር ፍሬ በሉ።
13እንዲህም ሆነ፥ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዓይኑን አንሥቶ ተመለከተ፥ እነሆም፥ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ ነበር፥ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ፦ ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን? አለው። 14እርሱም፦ አይደለሁም፥ እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቼአለሁ አለ። ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደና፦ ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድር ነው? አለው። 15የእግዚአብሔርም ሠራዊት አለቃ ኢያሱን፦ አንተ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው። ኢያሱም እንዲሁ አደረገ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ 5: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in