YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ኢያሱ 20

20
1እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2-3ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፦ ሳይወድድ ሳያውቅም ሰውን የገደለ ገዳይ እንዲሸሽባቸው በሙሴ እጅ የነገርኋችሁን መማፀኛ ከተሞችን ለዩ፥ ከደም ተበቃዩ መማፀኛ ይሆኑላችኋል። 4ከእነዚህም ከተሞች ወደ አንዲቱ ይሸሻል፥ በከተማይቱም በር አደባባይ ቆሞ በከተማይቱ ሽማግሌዎች ጆሮ ነገሩን ይናገራል፥ እነርሱም ወደ ከተማይቱ ይቀበሉታል፥ የሚቀመጥበትም ስፍራ ይሰጡታል። 5ደም ተበቃዩ ቢያሳድደው፥ አስቀድሞ ሳይጠላው ባልንጀራውን በስሕተት ስለ ገደለው ነፍሰ ገዳዩን በእጁ አሳልፈው አይስጡት። 6በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ፥ በዚያም ወራት ያለው ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያች ከተማ ይቀመጥ፥ ከዚያም ወዲያ ነፍሰ ገዳዩ ይመለሳል፥ ወደ ከተማውም ወደ ቤቱም ሸሽቶ ወደ ወጣበትም ከተማ ይገባል።
7በንፍታሌም ባለው በተራራማው አገር በገሊላ ቃዴስን፥ በኤፍሬምም ባለው በተራራማው አገር ሴኬምን፥ በይሁዳም ባለው በተራራማው አገር ኬብሮን የምትባለውን ቂርያትአርባቅን ለዩ። 8በዮርዳኖስም ማዶ ከኢያሪኮ ወደ ምሥራቅ ከሮቤል ነገድ በምድረ በዳው በደልዳላው ስፍራ ቦሶርን፥ ከጋድም ነገድ በገለዓድ ራሞትን፥ ከምናሴም ነገድ በባሳን ጎላንን ለዩ። 9በማኅበሩ ፊት እስኪቆም ድረስ በደም ተበቃዩ እጅ እንዳይሞት ሳያውቅ ሰውን የገደለ ወደዚያ እንዲሸሽ፥ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በመካከላቸውም ለሚቀመጥ መጻተኛ የተለዩ ከተሞች እነዚህ ናቸው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in