YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ኢዮብ 5

5
1አሁንም ጥራ፥ የሚመልስልህ አለን?
ከቅዱሳንስ ወደማናቸው ትዞራለህ?
2ሰነፉን ሰው ቍጣ ይገድለዋል፥
ሰነፉንም ቅንዓት ያጠፋዋል።
3ሰነፍ ሰው ሥር ሰድዶ አየሁት፥
ድንገትም መኖሪያውን ረገምሁ።
4ልጆቹም ከደኅንነት ርቀዋል፥
በበርም ውስጥ ተረግጠዋል፥
የሚታደጋቸውም የለም።
5የሰበሰበውንም ራብተኛ ይበላዋል፥
ከእሾህም ውስጥ እንኳ ያወጣዋል፥
የተጠማ ሀብታቸውን ዋጠ።
6ችግር ከትቢያ አይመጣም፥
መከራም ከመሬት አይበቅልም፥
7የአሞራ ግልገሎች ግን ወደ ላይ እየበረሩ ከፍ እንዲሉ፥
ሰው እንዲሁ ለመከራ ተወልዶአል።
8እኔ ግን እግዚአብሔርን እለምን ነበር፥
ነገሬንም ወደ እግዚአብሔር አቀርብ ነበር።
9የማይመረመረውን ታላቅ ነገርና
የማይቈጠረውን ተአምራት ያደርጋል።
10በምድር ላይ ዝናብን ይሰጣል፥
በእርሻም ላይ ውኃ ይልካል።
11የተዋረዱትን ወደ ላይ ያወጣል፥
ኀዘንተኞችንም ለደኅንነት ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል።
12እጃቸውም ምክራቸውን እንዳይፈጽም
የተንኰለኞችን አሳብ ከንቱ ያደርገዋል።
13ጠቢባንን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፥
የጠማሞችንም ምክር ይዘረዝራል።
14በቀን ጨለማን ያገኛሉ፥
በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳሉ ይርመሰመሳሉ።
15ድሀውንም ከአፋቸው ሰይፍ
ከኃያሉም እጅ ያድነዋል።
16ለምስኪኑም ተስፋ አለው፥
ክፋት ግን አፍዋን ትዘጋለች።
17እነሆ፥ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ምስጉን ነው፥
ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ።
18እርሱ ይሰብራል፥ ይጠግንማል፥
ያቈስላል፥ እጆቹም ይፈውሳሉ።
19በስድስት ክፉ ነገር ውስጥ ያድንሃል፥
በሰባትም ውስጥ ክፋት አትነካህም።
20በራብ ጊዜ ከሞት፥
በሰልፍም ከሰይፍ እጅ ያድንሃል።
21ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፥
ጥፋትም ሲመጣ አትፈራም።
22በጥፋትና በራብ ላይ ትስቃለህ፥
ከምድረ በዳ አራዊትም አትፈራም፥
23ቃል ኪዳንህ ከምድረ በዳ ድንጋይ ጋር ይሆናልና፥
የምድረ በዳም አራዊት ከአንተ ጋር ይስማማሉና።
24ድንኳንህም በሰላም እንዲሆን ታውቃለህ፥
በረትህን ትጐበኛለህ አንዳችም አይጐድልብህም።
25ዘርህም ታላቅ እንዲሆን፥
ትውልድህም እንደ ምድር ሣር እንዲሆን ታውቃለህ።
26በወራቱ የእህሉ ነዶ ወደ አውድማ እንዲገባ፥
በረጅም ዕድሜ ወደ መቃብር ትገባለህ።
27እነሆ፥ ይህችን መረመርን፥ የሰማነውም ይህ ነው፥
አንተ ግን አንዳች ሠርተህ እንደ ሆነ ለራስህ እወቀው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in