YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ኢዮብ 29

29
1ኢዮብም ምሳሌውን ይመስል ዘንድ ደገመ፥ እንዲህም አለ፦
2እግዚአብሔር ይጠብቀኝ እንደ ነበረው ጊዜ፥
እንደ ፊተኛው ወራት ምነው በሆንሁ!
3በራሴ ላይ መብራቱ በበራ ጊዜ፥
እኔም ጨለማውን አልፌ በብርሃኑ በሄድሁ ጊዜ፥
4በሙሉ ሰውነቴ እንደ ነበርሁ ጊዜ፥
እግዚአብሔር ድንኳኔን በጋረደ ጊዜ፥
5ሁሉን የሚችል አምላክ ከእኔ ጋር ገና ሳለ፥
ልጆቼም በዙሪያዬ ሳሉ፥
6መንገዴ በቅቤ ይታጠብ በነበረ ጊዜ፥
ድንጋዩ የዘይት ፈሳሽ ያፈስስልኝ በነበረ ጊዜ።
7ወደ ከተማይቱ በር በወጣሁ ጊዜ፥
በአደባባዩም ወንበሬን ባኖርሁ ጊዜ፥
8ጐበዛዝት እኔን አይተው ተሸሸጉ፥
ሽማግሌዎችም ተነሥተው ቆሙ።
9አለቆቹ ከመናገር ዝም አሉ፥
እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ጫኑ።
10የታላላቆቹም ድምፅ አረመመ፥
ምላሳቸውም በትናጋቸው ተጣጋ።
11የሰማችኝ ጆሮ አሞገሰችኝ፥
ያየችኝም ዓይን መሰከረችልኝ፥
12የሚጮኸውን ችግረኛ፥
ድሀ አደጉንና ረጂ የሌለውን አድኜ ነበርሁና።
13ለጥፋት የቀረበው በረከት በላዬ መጣ፥
የባልቴቲቱንም ልብ እልል አሰኘሁ።
14ጽድቅን ለበስሁ እርስዋም ለበሰችኝ፥
ፍርዴም እንደ መጐናጸፊያና እንደ ኵፋር ነበረ።
15ለዕውር ዓይን፥
ለአንካሳ እግር ነበርሁ።
16ለድሀው አባት ነበርሁ፥
የማላውቀውንም ሰው ሙግት መረመርሁ።
17የኃጢአተኛውን መንጋጋ ሰበርሁ፥
የነጠቀውንም ከጥርሱ ውስጥ አስጣልሁ።
18እኔም አልሁ፦ በልጆቼ መካከል እሞታለሁ፥
ዕድሜዬንም እንደ አሸዋ አበዛለሁ፥
19ሥሬ በውኃ ላይ ተዘርግቶአል፥
ጠልም በቅርንጫፌ ላይ ያድራል፥
20ክብሬ በእኔ ዘንድ ታድሶአል፥
ቀስቴም በእጄ ውስጥ ለምልሞአል።
21ሰዎች እኔን ሰምተው በትዕግሥት ተጠባበቁ፥
ምክሬንም ለማዳመጥ ዝም አሉ።
22ከቃሌ በኋላ አንዳች አልመለሱም፥
ንግግሬም በእነርሱ ላይ ተንጠባጠበ።
23ዝናብን እንደሚጠብቁ በትዕግሥት ጠበቁኝ፥
የጥቢን ዝናብ እንደሚሹ አፋቸውን ከፈቱ።
24እነርሱ ባልታመኑ ጊዜ ሳቅሁላቸው፥
የፊቴንም ብርሃን አላወረዱም።
25መንገዳቸውን መረጥሁ፥
እንደ አለቃ ሆኜ ተቀመጥሁ፥
ንጉሥ በሠራዊቱ መካከል እንደሚኖር፥
ኅዘነተኞችን እንደሚያጽናና ኖርሁ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in