መጽሐፈ ኢዮብ 15
15
1ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ፦
2በውኑ ጠቢብ ሰው እንደ ነፋስ በሆነ እውቀት ይመልሳልን?
በሆዱስ የምሥራቅን ነፋስ ይሞላልን?
3ከማይረባ ነገር፥
ወይስ ከማይጠቅም ንግግር ጋር ይዋቀሳልን?
4አንተም እግዚአብሔርን መፍራት ታፈርሳለህ፥
በእግዚአብሔር ፊት አምልኮን ታስቀራለህ።
5በደልህ አፍህን ያስተምረዋል፥
የተንኰለኞችንም አንደበት ትመርጣለህ።
6የሚፈርድብህ አፍህ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፥
ከንፈሮችህም ይመሰክሩብሃል።
7በውኑ መጀመሪያ የተወለድህ ሰው አንተ ነህን?
ወይስ ከተራሮች በፊት ተፀነስህን?
8የእግዚአብሔርንስ ምሥጢር ሰምተሃልን?
ወይስ ጥበብን ለብቻህ አድርገሃልን?
9እኛ የማናውቀውን አንተ የምታወቀው ምንድር ነው?
ከእኛ ዘንድስ የሌለው የምታስተውለው ምንድር ነው?
10በዕድሜ ከአባትህ የሚበልጡ
ሽበትም ያላቸው ሽማግሌዎችም ከእኛ ጋር አሉ።
11በውኑ የእግዚአብሔር ማጽናናት፥
በየውሃትም የተነገረህ ቃል ጥቂት ነውን?
12ልብህስ ለምን ይወስድሃል?
ዓይኖችህስ ለምን ይገለምጣሉ?
13በእግዚአብሔር ላይ መንፈስህን እስከ ማንሣት ደርሰህ፥
ይህንም ቃል ከአፍህ እስከ ማውጣት ደርሰህ።
14ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሰው ምንድር ነው?
ጻድቅስ ይሆን ዘንድ ከሴት የተወለደ ምንድር ነው?
15እነሆ፥ በቅዱሳኑ ስንኳ አይታመንም፥
ሰማያትም በፊቱ ንጹሐን አይደሉም።
16ይልቁንስ አስጸያፊና የረከሰ፥
ኃጢአትንም እንደ ውኃ የሚጠጣ ሰው ምንኛ ያንስ?
17-18ምድሪቱ ለብቻቸው ተሰጥታ የነበረች፥
19በመካከላቸውም እንግዳ ያልገባባቸው ጠቢባን
ከአባቶቻቸው ተቀብለው የተናገሩትን ያልሸሸጉትንም፥
እገልጥልሃለሁ፥ ስማኝ፥ ያየሁትንም እነግርሃለሁ።
20ክፉ ሰው ዕድሜውን ሙሉ፥
ለግፈኛ በተመደቡለት በዓመታት ሁሉ በሕመም ይጣጣራል።
21የሚያስደነግጥ ድምፅ በጆሮው ነው፥
በደኅንነቱም ሳለ ቀማኛ ይመጣበታል።
22ከጨለማ ተመልሶ እንዲወጣ አያምንም፥
ሰይፍም ይሸምቅበታል።
23ተቅበዝብዞም፦ ወዴት አለ? እያለ እንጀራ ይለምናል፥
የጨለማ ቀን እንደ ቀረበበት ያውቃል።
24መከራና ጭንቀት ያስፈራሩታል፥
ለሰልፍ እንደ ተዘጋጀ ንጉሥ ያሸንፉታል።
25እጁን በእግዚአብሔር ላይ ዘርግቶአልና፥
ሁሉንም በሚችል አምላክ ላይ ደፍሮአልና፥
26በደንዳና አንገቱና በወፍራሙ በጋሻው
ጕብጕብ እየሠገገ ይመጣበታልና፥
27በስብም ፊቱን ከድኖአልና፥
ስቡንም በወገቡ ላይ አድርጓልና፥
28በተፈቱም ከተሞች ውስጥ፥
ሰውም በሌለባቸው፥
ክምር ለመሆን በተመደቡ ቤቶች ውስጥ ተቀምጦአልና
29ባለጠጋ አይሆንም፥ ሀብቱም አይጸናም፥
ጥላውንም በምድር ላይ አይጥልም፥
30ከጨለማ አይወጣም፥
ነበልባሉም ቅርንጫፎቹን ያደርቃቸዋል፥
አበባዎቹም ይረግፋሉ።
31ዋጋው ከንቱ ነገር ይሆናልና
ራሱን እያሳተ በከንቱ ነገር አይታመን።
32ቀኑ ሳይደርስ ጊዜው ይፈጸማል፥
ቅርንጫፉም አይለመልምም።
33እንደ ወይን ያልበሰለውን ዘለላ ያረግፋል፥
እንደ ወይራ አበባውን ይጥላል።
34የዝንጉዎች ጉባኤ ሁሉ ለጥፋት ይሆናል፥
የጉቦ ተቀባዮችንም ድንኳን እሳት ትበላለች።
35ጉዳትን ይፀንሳሉ፥ በደልንም ይወልዳሉ፥
ሆዳቸውም ተንኰልን ያዘጋጃል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 15: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in