YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ኢዮብ 10

10
1ነፍሴ ሕይወቴን ሰለቸቻት፥
የኀዘን እንጕርጕሮዬን እለቅቀዋለሁ፥
በነፍሴም ምሬት እናገራለሁ።
2እግዚአብሔርን እንዲህ እለዋለሁ፦
አትፍረድብኝ፥ የምትከራከረኝ ለምን እንደ ሆነ ንገረኝ።
3ልታስጨንቅና የእጅህን ሥራ ልትንቅ
የኃጥአንንስ ምክር ልታበራ
በአንተ ዘንድ መልካም ነውን?
4በውኑ የሥጋ ዓይን አለህን?
ወይስ ሰው እንደሚያይ ታያለህን?
5-6ወይስ ክፋቴን ትፈላለግ ዘንድ፥
ኃጢአቴንም ትመረምር ዘንድ፥
ዘመንህ እንደ ሰው ዘመን ነውን?
ወይስ ዓመታትህ እንደ ሰው ዓመታት ናቸውን?
7ከዚህም በላይ በደለኛ እንዳልሆንሁ፥
ከእጅህም የሚያድን እንደሌለ አንተ ታውቃለህ።
8እጅህ ለወሰችኝ ሠራችኝም፥
ከዚያም በኋላ ዞረህ ታጠፋኝ ዘንድ ፈለግህ።
9እንደ ጭቃ አድርገህ እንደ ለወስኸኝ አስብ፥
ወደ ትቢያም ትመልሰኛለህን?
10በውኑ እንደ ወተት አላፈሰስኸኝምን?
እንደ እርጎስ አላረጋኸኝምን?
11ቁርበትና ሥጋ አለበስኸኝ፥
በአጥንትና በጅማትም አጠንከርኸኝ።
12ሕይወትና ቸርነት አደረግህልኝ፥
መጐብኘትህም መንፈሴን ጠበቀች።
13እነዚህንም ነገሮች በልብህ ውስጥ ሰወርህ፥
ይህ ሁሉ በአሳብህ እንዳለ አውቃለሁ።
14ኃጢአት ብሠራ አንተ ትመለከተኛለህ፥
ከኃጢአቴም ንጹሕ አታደርገኝም።
15በደለኛ ብሆን ወዮልኝ፥
ጻድቅም ብሆን ራሴን አላነሣም፥
ጕስቍልናን ተሞልቻለሁ፥
መከራዬንም ተመልክቻለሁ።
16ራሴም ከፍ ከፍ ቢል እንደ አንበሳ ታድነኛለህ፥
ተመልሰህም ድንቅ ነገር ታድርግብኛለህ።
17ምስክሮችህን ታድስብኛለህ፥
ቍጣህንም ታበዛብኛለህ፥
ጭፍራ በጭፍራ ላይ ትጨምርብኛለህ።
18ስለ ምን ከማኅፀን አወጣኸኝ?
ዓይን ሳያየኝ ምነው በሞትሁ።
19እንዳልነበረ በሆንሁ፥
ከማኅፀንም ወደ መቃብር በወሰዱኝ።
20የሕይወቴ ዘመን ጥቂት አይደለምን?
21ወደማልመለስበት ስፍራ፥
ወደ ጨለማና ወደ ሞት ጥላ ምድር፥
22እንደ ጨለማም ወደ ጨለመች፥
ሥርዓትም ወደሌለባት ወደ ሞት ጥላ፥
ብርሃንዋም እንደ ጨለማ ወደ ሆነ ምድር ሳልሄድ፥
ጥቂት እጽናና ዘንድ ተወኝ፥ ልቀቀኝም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in