YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኤርምያስ 37

37
1የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በይሁዳ ያነገሠው የኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ በኢዮአቄም ልጅ በኢኮንያን ፋንታ ነገሠ። 2እርሱም ሆነ ባሪያዎቹ የአገሩም ሕዝብ በነቢዩ በኤርምያስ እጅ የተናገረውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም።
3ንጉሡም ሴዴቅያስ፦ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ስለ እኛ ጸልይ ብሎ የሰሌምያን ልጅ ዮካልንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ ላከ። 4እርሱንም በግዞት ቤት ገና አላገቡትም ነበርና ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል ይወጣና ይገባ ነበር። 5የፈርዖንም ሠራዊት ከግብጽ ወጣ፥ ኢየሩሳሌምንም ከብበዋት የነበሩ ከለዳውያን ይህን ወሬ በሰሙ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ተመለሱ።
6የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 7የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከእኔ ትጠይቁ ዘንድ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት፦ እነሆ፥ ሊረዳችሁ የወጣው የፈርዖን ሠራዊት ወደ አገሩ ወደ ግብጽ ይመለሳል። 8ከለዳውያንም ተመልሰው ይህችን ከተማ ይዋጉአታል ይይዙአትማል በእሳትም ያቃጥሉአታል። 9እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አይሄዱምና፦ ከለዳውያን በእርግጥ ከእኛ ዘንድ ይሄዳሉ ብላችሁ ራሳችሁን አታታልሉ። 10እናንተም የሚዋጉትን የከለዳውያንን ሠራዊት ሁሉ ብትመቱት ኖሮ፥ ከእነርሱም የተወጉት ብቻ ቢቀሩ ኖሮ፥ ሁሉ እያንዳንዱ በድንኳኑ ተነሥቶ ይህችን ከተማ በእሳት ባቃጠሉአት ነበር።
11የከለዳውያንም ሠራዊት ከፈርዖን ሠራዊት ፊት የተነሣ ከኢየሩሳሌም በተመለሰ ጊዜ፥ 12ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል የርስቱን እድል ፈንታ ከዚያ ይቀበል ዘንድ ወደ ብንያም አገር ሊሄድ ከኢየሩሳሌም ወጣ። 13በብንያምም በር በነበረ ጊዜ የሐናንያ ልጅ የሰሌምያ ልጅ የሪያ የተባለ የዘበኞች አለቃ በዚያ ነበረ፥ እርሱም፦ ወደ ከለዳውያን መኰብለልህ ነው ብሎ ነቢዩን ኤርምያስን ያዘው። 14ኤርምያስም፦ ሐሰት ነው፥ ወደ ከለዳውያን መኰብለሌ አይደለም አለ፥ እርሱ ግን አልሰማውም፥ የሪያም ኤርምያስን ይዞ ወደ አለቆች አመጣው። 15አለቆችም ተቈጥተው ኤርምያስን መቱት፥ የጸሐፊውንም የዮናታንን ቤት የግዞት ቤት አድርገውት ነበርና በዚያ አኖሩት።
16ኤርምያስም ወደ ጕድጓድ ቤት ወደ ጓዳዎቹ ገባ፥ ኤርምያስም በዚያ ብዙ ቀን ከተቀመጠ በኋላ፥ 17ንጉሡ ሴዴቅያስ ልኮ አስመጣው፥ ንጉሡም በቤቱ፦ በውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ ቃል አለን? ብሎ በቈይታ ጠየቀው። ኤርምያስም፦ አዎን አለ። ደግሞም፦ በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፈህ ትሰጣለህ አለ። 18ኤርምያስም ደግሞ ንጉሡን ሴዴቅያስን እንዲህ አለው፦ በግዞት ቤት የጣላችሁኝ አንተን ወይስ ባሪያዎችህን ወይስ ሕዝብህን ምን በድያችሁ ነው? 19የባቢሎን ንጉሥ በእናንተና በዚህች አገር አይመጣባችሁም ብለው ትንቢት ይናገሩላችሁ የነበሩ ነቢያቶቻችሁ ወዴት አሉ? 20ንጉሡ ጌታዬ ሆይ፥ እንድትሰማኝ አሁን እለምንሃለሁ፥ እባክህ፥ ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ፥ በዚያ እንዳልሞት ወደ ጸሐፊው ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ። 21ንጉሡም ሴዴቅያስ አዘዘ፥ ኤርምያስንም በግዞት ቤት አደባባይ አኖሩት፥ እንጀራም ሁሉ ከከተማ እስኪጠፋ ድረስ ዕለት ዕለት አንድ አንድ እንጀራ ከጋጋሪዎች መንገድ ይሰጡት ነበር። እንዲሁም ኤርምያስ በግዞት ቤት አደባባይ ተቀምጦ ነበር።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in