ትንቢተ ኤርምያስ 30
30
1ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የነገርሁህን ቃል ሁሉ በመጽሐፍ ጻፍ። 3እነሆ፥ የሕዝቤን የእስራኤልንና የይሁዳን ምርኮ የምመልስበት ዘመን ይመጣልና፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠኋት ምድር እመልሳቸዋለሁ፥ እነርሱም ይገዙአታል።
4እግዚአብሔር ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 5እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ የሚያስፈራ ድምፅ ሰምተናል፥ የፍርሃት ነው እንጂ የሰላም አይደለም። 6ጠይቁ፥ ወንድ ይወልድ እንደ ሆነ ተመልከቱ፥ ስለ ምን ሰው ሁሉ እንደ ወላድ እጁን በወገቡ ላይ አድርጎ ፊቱም ሁሉ ወደ ጥቁረት ተለውጦ አየሁ? 7ወዮ! ያ ቀን ታላቅ ነውና፥ እርሱንም የሚመስል የለምና፥ ያ የያዕቆብ መከራ ዘመን ነው፥ ነገር ግን ከእርሱ ይድናል። 8በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ቀንበርን ከአንገትህ እሰብራለሁ፥ እስራትህንም እበጥሳለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ለሌላ አትገዛም፥ 9ለአምላካቸው ለእግዚአብሔርም ለማስነሣላቸው ለንጉሣቸው ለዳዊትም ይገዛሉ እንጂ ሌሎች አሕዛብ እንደ ገና አይገዙአቸውም።
10እነሆ፥ አንተን ከሩቅ ዘርህንም ከምርኮ አገር አድናለሁና ባሪያዬ ያዕቆብ ሆይ፥ አትፍራ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ አንተም እስራኤል ሆይ፥ አትደንግጥ፥ ያዕቆብም ይመለሳል ያርፍማል ተዘልሎም ይቀመጣል፥ ማንም አያስፈራውም። 11አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና፥ ይላል እግዚአብሔር፥ አንተንም የበተንሁባቸውን አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁ፥ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፥ በመጠን እቀጣሃለሁ፥ ያለ ቅጣትም ከቶ አልተውህም።
12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስብራትህ የማይፈወስ ቍስልህም ክፉ ነው። 13ትጠገን ዘንድ ክርክርህን የሚፈርድልህ የለም፥ ቍስልህንም የሚፈውስ መድኃኒት የለህም። 14ውሽሞችህ ሁሉ ረስተውሃል አይፈልጉህምም፥ በደልህ ታላቅ ስለሆነ ኃጢአትህም ስለ በዛ፥ በጠላት ማቍሰልና በጨካኝ ቅጣት አቍስዬሃለሁና። 15ሕመምህ የማይፈወስ ሆኖአልና ስለ ስብራትህ ለምን ትጮኻለህ? በደልህ ታላቅ ስለሆነ ኃጢአትህም ስለ በዛ፥ ይህን አድርጌብሃለሁ። 16ስለዚህ የሚውጡህ ሁሉ ይዋጣሉ፥ ጠላቶችህም ሁላቸው ይማረካሉ፥ የዘረፉህም ይዘረፋሉ፥ የበዘበዙህንም ሁሉ ለመበዝበዝ አሳልፌ እሰጣለሁ። 17እኔ ጤናህን እመልስልሃለሁ ቍስልህንም እፈውሳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ማንም የማይሻት፥ የተጣለች ጽዮን ብለው ጠርተውሻልና።
18እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፥ ለማደሪያውም እራራለሁ፥ ከተማይቱም በጉብታዋ ላይ ትሠራለች፥ አዳራሹም እንደ ዱሮው የሰው መኖሪያ ይሆናል። 19ከእርሱም ዘንድ የምስጋናና የዘፋኞች ድምፅ ይወጣል፥ እኔም አበዛቸዋለሁ አያንሱምም፥ እኔም አከብራቸዋለሁ ታናሽም አይሆኑም። 20ልጆቻቸውም እንደ ቀድሞ ይሆናሉ፥ ማኅበራቸውም በፊቴ ጸንቶ ይኖራል፥ የሚያስጨንቋቸውንም ሁሉ እቀጣለሁ። 21አለቃቸው ከእነርሱ ውስጥ ይሆናል፥ ገዥአቸውም ከመካከላቸው ይወጣል፥ እኔ አቀርበዋለሁ እርሱም ይቀርባል፥ ይህስ ባይሆን ወደ እኔ ለመቅረብ የሚደፍር ማን ነው? ይላል እግዚአብሔር። 22እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።
23እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዐውሎ ነፋስ፥ እርሱም ቍጣው፥ የሚያገለባብጥ ዐውሎ ነፋስ ወጥቶአል፥ የዓመፀኞችንም ራስ ይገለባብጣል። 24የእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም፥ በኋለኛው ዘመን ታስተውሉታላችሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 30: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in