YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኤርምያስ 10

10
1እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ የተናገረውን ቃል ስሙ። 2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአሕዛብን መንገድ አትማሩ ከሰማይ ምልክትም አትፍሩ፥ አሕዛብ ይፈሩታልና። 3የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፥ ዛፍ ከዱር ይቈረጣል፥ በሠራተኛም እንጅ በመጥረቢያ ይሠራል። 4በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፥ እንዳይናወጥም በችንካርና በመዶሻ ይቸነክሩታል። 5እንደ ተቀረጸ ዓምድ ናቸው እነርሱም አይናገሩም፥ መራመድም አይቻላቸውምና ይሸከሙአቸዋል። ክፉ መሥራትም አይቻላቸውምና፥ ደግምም መልካም ይሠሩ ዘንድ አይችሉምና አትፍሩአቸው።
6አቤቱ፥ እንደ አንተ ያለ የለም፥ አንተ ታላቅ ነህ ስምህም በኃይል ታላቅ ነው። 7የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፥ በአሕዛብ ጥበበኞች ሁሉ መካከል በመንግሥታቸውም ሁሉ እንደ አንተ ያለ ስለሌለ፥ አንተን መፍራት ይገባልና አንተን የማይፈራ ማን ነው? 8በአንድ ጊዜ ሰንፈዋል፥ ደንቍረውማል፥ ጣዖታት የሚያስተምሩት የእንጨት ነገር ብቻ ነው። 9የሠራተኛና የአንጥረኛ እጅ ሥራ የሆነ ከተርሴስ ጥፍጥፍ ብር ከአፌዝም ወርቅ ይመጣል፥ ልብሳቸውም ሰማያዊና ቀይ ግምጃ ነው፥ ሁሉም የብልሃተኞች ሥራ ናቸው። 10እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፥ እርሱም ሕያው አምላክና የዘላለም ንጉሥ ነው፥ ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፥ አሕዛብም መዓቱን አይችሉም።
11እናንተም፦ ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ እነዚህ አማልክት ከምድር ላይ ከሰማይም በታች ይጠፋሉ ትሉአቸዋላችሁ።
12ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው። 13ድምፁን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይሰበሰባሉ፥ ከምድርም ዳር ደመናትን ከፍ ያደርጋል፥ ለዝናቡም መብረቅን ያደርጋል፥ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል። 14ሰው ሁሉ እውቀት አጥቶ ሰንፎአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፥ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስትንፋስም የላቸውምና። 15እነርሱ ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው፥ በተጐበኙ ጊዜ ይጠፋሉ። 16የያዕቆብ እድል ፈንታ እንደ እነዚህ አይደለም፥ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነውና፥ እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነውና፥ ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
17በምሽግ ውስጥ የተቀመጥሽ ሆይ፥ ዕቃሽን ከመሬት ሰብስቢ፥ 18እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ በምድሪቱ የሚኖሩትን እስኪሰማቸው ድረስ በዚህ ጊዜ እወነጭፋቸዋለሁ፥ አስጨንቃቸውማለሁ።
19ስለ ስብራቴ ወዮልኝ! ቍስሌም ክፉ ነው፥ እኔ ግን፦ በእውነት የመከራ ቍስሌ ነው እርሱንም መሸከም ይገባኛል አልሁ። 20ድንኳኔ ተበዘበዘ አውታሬም ሁሉ ተቈረጠ፥ ልጆቼም ከእኔ ወጥተው አይገኙም፥ ድንኳኔንም ከእንግዲህ ወዲህ የሚዘረጋ መጋረጃዎችንም የሚያነሣ የለም። 21እረኞች ሰንፈዋልና፥ እግዚአብሔርን አልጠየቁትምና አልተከናወነላቸውም፥ መንጎቻቸውም ሁሉ ተበትነዋል። 22የወሬን ድምፅ ስሙ፥ እነሆም፥ የይሁዳን ከተሞች ባድማና የቀበሮ ማደሪያ ያደርጋቸው ዘንድ ከሰሜን ምድር ጽኑ ሽብር መጥቶአል።
23አቤቱ፥ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፥ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም። 24አቤቱ፥ ቅጣኝ፥ ነገር ግን እንዳታዋርደኝ በመጠን ይሁን እንጂ በቍጣ አይሁን። 25ያዕቆብን በልተውታልና፥ ውጠውትማልና፥ አጥፍተውትማልና፥ ማደሪያውንም አፍርሰዋልና በማያውቁህ አሕዛብ ስምህንም በማይጠሩ ወገኖች ላይ መዓትህን አፍስስ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in