YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ መሳፍንት 5

5
1በዚያም ቀን ዲቦራና የአቢኒኤም ልጅ ባርቅ እንዲህ ብለው ተቀኙ፦
2በእስራኤል ውስጥ መሪዎች ስለ መሩ፥
ሕዝቡም ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ስለ ሰጡ፥
እግዚአብሔርን አመስግኑ።
3ነገሥታት ሆይ፥ ስሙ፥
መኳንንት ሆይ፥ አድምጡ፥
እኔ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፥
ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ።
4አቤቱ፥ ከሴይር በወጣህ ጊዜ፥
ከኤዶምያስም ሜዳ በተራመድህ ጊዜ፥
ምድሪቱ ተናወጠች፥ ሰማያቱም አንጠበጠቡ፥
ደመናትም ደግሞ ውኃን አንጠበጠቡ።
5ተራሮች ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ ቀለጡ፥
ያም ሲና ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ።
6በዓናት ልጅ በሰሜጋር ዘመን፥
በኢያዔል ዘመን መንገዶች ተቋረጡ፥
መንገደኞች በስርጥ መንገድ ይሄዱ ነበር።
7አንቺ፥ ዲቦራ፥ እስክትነሽ ድረስ፥
ለእስራኤልም እናት ሆነሽ እስክትነሽ ድረስ፥
ኃያላን በእስራኤል ዘንድ አነሱ፥ አለቁም።
8አዲሶች አማልክትን መረጡ፥
በዚያ ጊዜ ሰልፍ በበሮች ሆነ፥
በአርባ ሺህ በእስራኤል ዘንድ ጦርና ጋሻ አልታየም።
9ልቤ ወደ እስራኤል አለቆች ነው፥
በሕዝቡ መካከል ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ወደ ሰጡት፥
እግዚአብሔርን አመስግኑ።
10በነጫጭ አህዮች ላይ የምትጫኑ፥
በወላንሳ ላይ የምትቀመጡ፥
በመንገድም የምትሄዱ፥ ተናገሩ።
11በማጠጫው መካከል ካሉት ከቀስተኞች ጩኸት ርቀው፥
በዚያ የእግዚአብሔርን ጽድቅ፥
በእስራኤል ላይ የግዛቱን ጽድቅ ይጫወታሉ፥
ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ በሮች ወረዱ።
12ንቂ፥ ንቂ፥ ዲቦራ ሆይ፥
ንቂ፥ ንቂ፥ ቅኔውን ተቀኚ፥
ባርቅ ሆይ፥ ተነሣ፥
የአቢኒኤም ልጅ ሆይ፥ ምርኮህን ማርክ።
13በዚያ ጊዜ የቀሩት ወደ ኃያላኑና ወደ ሕዝቡ ወረዱ፥
እግዚአብሔርም ስለ እኔ በኃያላን ላይ ወረደ።
14በአማሌቅ ዘንድ ሥር የነበራቸው እነርሱ ከኤፍሬም፥
ብንያም ሆይ፥ በሕዝብህ መካከል ከአንተ በኋላ ወረዱ፥
አለቆች ከማኪር፥ የንጉሥንም ዘንግ የሚይዙ ከዛብሎን ወረዱ።
15የይሳኮርም አለቆች ከዲቦራ ጋር ነበሩ፥
ይሳኮርም እንደ ባርቅ ነበረ፥
ከእግሩ በኋላ ወደ ሸለቆው ቸኰሉ፥
በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ብዙ የልብ ማመንታት ነበረ።
16መንጎች ሲያፍዋጩ ለመስማት
በበጎች ጉረኖ መካከል ለምን ተቀመጥህ?
በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ታላቅ የልብ ምርምር ነበረ።
17ገለዓድ በዮርዳኖስ ማዶ ተቀመጠ፥
ዳንም ለምን በመርከብ ውስጥ ቀረ?
አሴርም በባሕሩ ዳር ተቀመጠ፥
በወንዞቹም ዳርቻ ዐረፈ።
18ዛብሎን ነፍሱን ወደ ሞት ያሳለፈ ሕዝብ ነው፥
ንፍታሌምም በአገሩ ኮረብታ ላይ ነው።
19ነገሥታት መጡ፥ ተዋጉም፥
በዚያ ጊዜ በመጊዶ ውኆች አጠገብ በታዕናክ
የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፥
የብር ዘረፋም አልወሰዱም።
20ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፥
በአካሄዳቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ።
21ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥
የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው።
ነፍሴ ሆይ፥ በኃይል እርገጪ።
22ከኃያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣ
የፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ።
23የእግዚአብሔር መልአክ፦ ሜሮዝን እርገሙ፥
እግዚአብሔርን በኃያላን መካከል ለመርዳት፥
እግዚአብሔርን ለመርዳት አልመጡምና
የተቀመጡባትን ሰዎች ፈጽማችሁ እርገሙ አለ።
24የቄናዊው የሔቤር ሚስት ኢያዔል
ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፥
በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን።
25ውኃ ለመነ፥ ወተትም ሰጠችው፥
በተከበረ ዳካ እርጎ አቀረበችለት።
26እጅዋን ወደ ካስማ፥
ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፥
በመዶሻውም ሲሣራን መታች፥ ራሱንም ቸነከረች፥
ጆሮግንዱንም በሳች፥ ጎዳችውም።
27በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ ተኛ፥
በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥
በተደፋበት ስፍራ በዚያ ወድቆ ሞተ።
28ከመስኮት ሆና ተመለከተች፥
የሲሣራ እናት በሰቅሰቅ ዘልቃ፦
ስለ ምን ለመምጣት ሰረገላው ዘገየ?
ስለ ምንስ የሰረገላው መንኰራኵር ቈየ? ብላ ጮኸች።
29ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፥
እርስዋ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች፦
30ምርኮ አግኝተው የለምን? ተካፍለውስ የለምን?
ለእያንዳንዱ ሰው ምርኮ አንዲት ወይም ሁለት ቈነጃጅት፥
ለሲሣራ ምርኮ ልዩ ልዩ ያለው ልብስ፥
በአንገትጌ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጕርጉር ልብስ።
31አቤቱ፥ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፥
ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፥ እንዲሁ ይሁኑ። ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in