YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኢሳይያስ 11

11
1ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፥ ከሥሩም ቍጥቋጥ ያፈራል። 2የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። 3እግዚአብሔርን በመፍራት ደስታውን ያያል። ዓይኑም እንደምታይ አይፈርድም፥ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም፥ 4ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፥ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል፥ በአፉም በትር ምድርን ይመታል፥ በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል። 5የወገቡ መታጠቂያ ጽድቅ፥ የጎኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል። 6ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፥ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፥ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፥ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል። 7ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፥ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ያርፋሉ፥ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። 8የሚጠባውም ሕፃን በእባብ ጕድጓድ ላይ ይጫወታል፥ ጡት የጣለውም ሕፃን በእፉኝት ቤት ላይ እጁን ይጭናል። 9በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጐዱም አያጠፉምም፥ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና። 10በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ለአሕዛብ ምልክት ሊሆን የቆመውን የእሴይን ሥር አሕዛብ ይፈልጉታል፥ ማረፊያውም የተከበረ ይሆናል። 11በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ የቀረውን የሕዝቡን ቅሬታ ከአሦርና ከግብፅ፥ ከጳትሮስና ከኢትዮጵያ፥ ከኤላምና ከሰናዖር ከሐማትም፥ ከባሕርም ደሴቶች ይመልስ ዘንድ ጌታ እንደገና እጁን ይገልጣል። 12ለአሕዛብም ምልክትን ያቆማል፥ ከእስራኤልም የተጣሉትን ይሰበስባል፥ ከይሁዳም የተበተኑትን ከአራቱ የምድር ማዕዘኖች ያከማቻል። 13የኤፍሬምም ምቀኝነት ይርቃል፥ ይሁዳንም የሚያስጨንቁ ይጠፋሉ፤ ኤፍሬምም በይሁዳ አይቀናም፥ ይሁዳም ኤፍሬምን አያስጨንቅም። 14በምዕራብም በኩል በፍልስጥኤማውያን ጫንቃ ላይ እየበረሩ ይወርዳሉ፥ የምሥራቅንም ልጆች በአንድነት ይበዘብዛሉ፥ በኤዶሚያስና በሞአብም ላይ እጃቸውን ይዘረጋሉ፥ የአሞንም ልጆች ለእነርሱ ይታዘዛሉ። 15እግዚአብሔርም የግብጽን ባሕር ያጠፋል፥ በትኩሱም ነፋስ እጁን በወንዙ ላይ ያነሣል፥ ሰባት ፈሳሾችንም አድርጎ ይመታዋል፥ ሰዎችም በጫማቸው እንዲሻገሩ ያደርጋቸዋል። 16ከግብጽም በወጣ ጊዜ ለእስራኤል እንደነበረ፥ የቀረው ለሕዝቡ ቅሬታ ከአሦር ጎዳና ይሆናል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in