YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ሕዝቅኤል 18

18
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2ስለ እስራኤል ምድር፦ አባቶች ጨርቋ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ ብላችሁ የምትመስሉት ምሳሌ ምንድር ነው? 3እኔ ሕያው ነኝና እንግዲህ ወዲህ ይህን ምሳሌ በእስራኤል ዘንድ አትመስሉትም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 4እነሆ፥ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው፥ የአባት ነፍስ የእኔ እንደ ሆነች ደግሞ የልጅ ነፍስ የእኔ ናት፥ ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች። 5ሰውም ጻድቅ ቢሆን ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፥ 6በተራራም ላይ ባይበላ ዓይኞቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ አደፍም ወዳለባት ሴት ባይቀርብ፥ 7ሰውንም ባያስጨንቅ ለባለ ዕዳም መያዣውን ቢመልስ ፈጽሞም ባይቀማ ከእንጀራውም ለተራበ ቢሰጥ የተራቈተውንም በልብስ ቢያለብስ፥ 8በአራጣ ባያበድር፥ ትርፎቻም ባይወስድ፥ እጁንም ከኃጢአት ቢመልስ፥ በሰውና በሰው መካከልም የእውነትን ፍርድ ቢፈርድ፥ በትእዛዜም ቢሄድ፥ 9እውነትንም ለማድረግ ፍርዴን ቢጠብቅ፥ እርሱ ጻድቅ ነው፥ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
10እርሱም ቀማኛና ደም አፍሳሽ ልጅ ከዚህም ሁሉ አንዳቸውን የሚያደርገውን ቢወልድ፥ 11እርሱም ጻድቅ አባቱ የሠራውን ሁሉ ባይሠራ በተራራም ላይ ቢበላ የባልንጀራውንም ሚስት ቢያረክስ፥ 12ድሀውንና ችግረኛውንም ቢያስጨንቅ ቢቀማም መያዣውንም ባይመልስ ዓይኖቹንም ወደ ጣዖታት ቢያነሣ ርኩስን ነገር ቢያደርግ፥ 13በአራጣ ቢያበድር፥ ትርፎቻም ቢወስድ፥ በውኑ እርሱ በሕይወት ይኖራልን? በሕይወት አይኖርም፥ ይህን ርኵሰት ሁሉ አድርጎአልና ፈጽሞ ይሞታል፥ ደሙ በላዩ ላይ ይሆናል።
14እነሆም፥ ልጅ ቢወልድ፥ እርሱም አባቱ የሠራውን ኃጢአት አይቶ ቢፈራ እንዲህም ባይሠራ፥ 15በተራራ ላይ ባይበላ ዓይኖቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ፥ 16ሰውንም ባያስጨንቅ መያዣውን ባይወስድ ባይቀማም ከእንጀራውም ለተራበ ቢሰጥ ለተራቈተውም ልብስን ቢያለብስ፥ 17እጁንም ድሀን ከመበደል ቢመልስ አራጣን ትርፎቻንም ባይወስድ ፍርዴንም ቢያደርግ በትእዛዜም ቢሄድ፥ እርሱ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ በአባቱ ኃጢአት አይሞትም። 18አባቱ ግን ፈጽሞ በድሎአልና፥ ወንድሙንም ቀምቶአልና፥ በሕዝቡም መካከል ክፉን ነገር አድርጎአልና እነሆ፥ እርሱ በበደሉ ይሞታል።
19እናንተ ግን፦ ልጅ የአባቱን ኃጢአት ስለ ምን አይሸከምም? ትላላችሁ። ልጅ ፍርድንና ቅን ነገርን ባደረገ ትእዛዜንም ሁሉ በጠበቀና ባደረገ ጊዜ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል። 20ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች፥ ልጅ የአባቱን ኃጢአት አይሸከምም፥ አባትም የልጁን ኃጢአት አይሸከምም፥ የጻድቁ ጽድቅ በራሱ ላይ ይሆናል፥ የኃጢአተኛውም ኃጢአት በራሱ ላይ ይሆናል።
21ኃጢአተኛውም ካደረጋት ኃጢአት ሁሉ ቢመለስ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቅ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 22የበደለው በደል ሁሉ አይታሰብበትም፥ በሠራው ጽድቅ በሕይወት ይኖራል። 23በውኑ ኃጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ ከመንገዱስ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን? 24ጻድቁ ግን ከጽድቁ ቢመለስ ኃጢአትንም ቢሠራ ኃጢአተኛውም እንደሚያደርገው ርኵሰት ሁሉ ቢያደርግ፥ በሕይወት ይኖራልን? የሠራት ጽድቅ ሁሉ አትታሰብለትም፥ ባደረገው ዓመፅና በሠራት ኃጢአት በዚያች ይሞታል።
25እናንተ ግን፦ የጌታ መንገድ የቀናች አይደለችም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እንግዲህ ስሙ፥ በውኑ መንገዴ የቀናች አይደለችምን? ይልቅስ የእናንተ መንገድ ያልቀናች አይደለችምን? 26ጻድቁ ከጽድቁ ቢመለስ፥ ኃጢአትንም በሠራ ጊዜ፥ በዚያም ቢሞት፥ እርሱ ባደረገው በደል ይሞታል። 27ኃጢአተኛውም ከሠራው ኃጢአት ቢመለስ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ነፍሱን ይጠብቃል። 28አስቦ ከሠራው በደል ሁሉ ተመልሶአልና ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 29ነገር ግን የእስራኤል ቤት፦ የጌታ መንገድ የቀናች አይደለችም ይላል። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በውኑ መንገዴ የቀናች አይደለችምን? ይልቅስ የእናንተ መንገድ ያልቀናች አይደለችምን? 30የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለዚህ እንደ መንገዱ በየሰዉ ሁሉ እፈርድባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር ንስሐ ግቡ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ። 31የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፥ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ ምን ትሞታላችሁ? 32የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in