ኦሪት ዘጸአት 2
2
የሙሴ መወለድ
1ከሌዊ ወገንም አንድ ሰው ሄዶ የሌዊን ልጅ አገባ። 2ሴቲቱም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ መልካምም እንደሆነ ባየች ጊዜ ሦስት ወር ሸሸገችው። 3ደግሞም ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ፥ የደንገል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም አኖረችበት፤ በወንዝም ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው። 4እኅቱም የሚደርስበትን ታውቅ ዘንድ በሩቅ ቆማ ትመለከት ነበር። 5የፈርዖንም ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ ወረደች፤ ደንገጥሮችዋም በወንዝ ዳር ይሄዱ ነበር፤ ሣጥኑንም በቄጠማ ውስጥ አየች፤ ደንገጥሩዋንም ልካ አስመጣችው። 6በከፈተችውም ጊዜ ሕፃኑን አየች፤ እነሆም ሕፃኑ ያለቅስ ነበር፤ አዘነችለትም፤ “ይህ ከዕብራውያን ልጆች አንድ ነው፤” አለች። 7እኅቱም ለፈርዖን ልጅ፦ “ሕፃኑን ታጠባልሽ ዘንድ ሄጄ የምታጠባት ሴት ከዕብራውያን ሴቶች ልጥራልሽን?” አለቻት፤ 8የፈርዖንም ልጅ፦ “ሂጂ” አለቻት፤ ብላቴናይቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ጠራች። 9የፈርዖንም ልጅ፦ “ይህን ሕፃን ወስደሽ አጥቢልኝ፤ ዋጋሽንም እሰጥሻለሁ፤” አለቻት። ሴቲቱም ሕፃኑን ወስዳ አጠባችው። 10ሕፃኑም አደገ፤ ወደ ፈርዖንም ልጅ ዘንድ አመጣችው፤ ለእርስዋም ልጅ ሆነላት። “እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና” ስትልም ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው።#2፥10 “ሙሴ” በዕብራይስጥ “ማውጣት” ማለት ነው።
የሙሴ ወደ ምድያም መኰብለል
11በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ ጎበዝ በሆነ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ፤ የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ፤ የግብፅም ሰው የወንድሞቹን የዕብራውያንን ሰው ሲመታ አየ። 12ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፤ ማንንም አላየም፤ ግብፃዊውንም ገደለ፤ በአሸዋም ውስጥ ሸሸገው። 13በሁለተኛውም ቀን ወጣ፤ ሁለቱም የዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፤ በዳዩንም፦ “ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ?” አለው። 14ያም፦ “በእኛ ላይ አንተን አለቃ ወይስ ዳኛ ማን አደረገህ? ወይስ ግብፃዊውን እንደገደልኸው ልትገድለኝ ትሻለህን?” አለው። ሙሴም፦ “በእውነት ይህ ነገር ታውቆአል” ብሎ ፈራ። 15ፈርዖንም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኰበለለ፤ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፤ በውኃም ጉድጓድ አጠገብ ዐረፈ። 16ለምድያምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም መጥተው ውኃ ቀዱ፤ የአባታቸውንም በጎች ሊያጠጡ የውኃውንም ገንዳ ሞሉ። 17እረኞችም መጥተው ገፉአቸው፤ ሙሴ ግን ተነሥቶ ረዳቸው፤ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው። 18ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤልም በመጡ ጊዜ፦ “ስለ ምን ዛሬ ፈጥናችሁ መጣችሁ?” አላቸው። 19እነርሱም፦ “አንድ የግብፅ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፤ ደግሞም ቀዳልን፤ በጎቻችንንም አጠጣ፤” አሉ። 20ልጆቹንም፦ “እርሱ ወዴት ነው? ለምንስ ያንን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት፤ እንጀራም ይብላ፤” አላቸው። 21ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ወደደ፤ ልጁንም ሲፓራን ለሙሴ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው። 22ወንድ ልጅም ወለደች፤ “በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ” ሲል ስሙን ጌርሳም ብሎ ጠራው። 23ከዚያም ከብዙ ቀን በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ ሞተ፤ የእስራኤልም ልጆች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፤ ጮኹም፤ ስለባርነታቸውም ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። 24እግዚአብሔርም የለቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፤ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አሰበ። 25እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች አየ፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ያለውን ነገር አወቀ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 2: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in