YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘጸአት 18

18
1የምድያምም ካህን የሙሴ አማት ዮቶር እግዚአብሔር ለሙሴና ለሕዝቡ ለእስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ እግዚአብሔርም እስራኤልን ከግብፅ እንዳወጣ ሰማ። 2በዚያን ጊዜ የሙሴ አማት ዮቶር መልሶአት የነበረውን የሙሴን ሚስት ሲፓራን ሁለቱንም ልጆቿን ወሰደ። 3ከእነርሱ የአንደኛው ስም ጌርሳም ነበረ፤ አባቱ፦ በሌላ አገር ስደተኛ ነበርሁ ብሎአልና፤ 4የሁለተኛውም ስም አልዓዛር ነበረ፦ የአባቴ አምላክ ረዳኝ፥ ከፈርዖንም ሰይፍ አዳነኝ ብሎአልና። 5የሙሴ አማት ዮቶርም ከልጆቹና ከሚስቱ ጋር በእግዚአብሔር ተራራ አጠገብ በምድረ በዳ ወደ ሰፈረ ወደ ሙሴ መጣ። 6ሙሴንም፦ እኔ አማትህ ዮቶር፥ ሚስትህም፥ ከእርስዋም ጋር ሁለቱ ልጆችዋ መጥተንልሃል አለው። 7ሙሴም አማቱን ሊገናኝ ወጣ፥ ሰገደም፥ ሳመውም፤ እርስ በርሳቸውም ደኅንነታቸውን ተጠያየቁ፥ ወደ ድንኳኑም ገቡ። 8ሙሴም እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብፃውያን ላይ ስለ እስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ በመንገድም ያገኛቸውን ድካም ሁሉ፥ እግዚአብሔርም እንዳዳናቸው ለአማቱ ነገረው። 9ዮቶርም እግዚአብሔር ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ሁሉ፥ ከግብፃውያንም እጅ ስላዳናቸው ደስ አለው። 10ዮቶርም፦ ከግብፃውያንና ከፈርዖን እጅ ያዳናችሁ፥ ከግብፃውያንም እጅ ሕዝቡን ያዳነ እግዚአብሔር ይባረክ። 11ትዕቢት ባደረጉባቸው ነገር እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ እንዲበልጥ አሁን አወቅሁ አለ። 12የሙሴ አማት ዮቶርም የሚቃጠል መስዋዕትንና ሌላ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር ወሰደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከሙሴ አማት ጋር እንጀራ ሊበሉ አሮን የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ። 13እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ሙሴ በሕዝቡ ሊፈርድ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም በሙሴ ፊት ከጥዋት እስከ ማታ ድረስ ቆመው ነበር። 14የሙሴም አማት በሕዝቡ ያደረገውን ሁሉ ባየ ጊዜ፦ ይህ በሕዝቡ የምታደርገው ምንድር ነው? ሕዝቡ ሁሉ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ በዙሪያህ ቆመው ሳሉ አንተ ብቻህን ስለ ምን ተቀምጠሃል? አለው። 15ሙሴም አማቱን፦ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ 16ነገርም ቢኖራቸው ወደ እኔ ይመጣሉ፥ በዚህና በዚያ ሰውም መካከል እፈርዳለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓትና ሕግ አስታውቃቸዋለሁ አለው። 17የሙሴም አማት አለው፦ አንተ የምታደርገው ይህ ነገር መልካም አይደለም። 18ይህ ነገር ይከብድብሃልና አንተ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፤ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም። 19አሁንም እመክርሃለሁና ቃሌን ስማ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አንተ በእግዚአብሔር ፊት ለሕዝቡ ሁን፥ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አድርስ፤ 20ሥርዓቱንም ሕጉንም አስተምራቸው፥ የሚሄዱበትን መንገድ የሚያደርጉትንም ሥራ ሁሉ አሳያቸው። 21አንተም ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎችን፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥ የታመኑ፥ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ፤ ከእነርሱም የሺህ አለቆችን፥ የመቶ አለቆችን፥ የአምሳ አለቆችን፥ የአሥርም አለቆችን ሹምላቸው። 22በሕዝቡ ላይ ሁልጊዜ ይፍረዱ፤ አውራውን ነገር ሁሉ ወደ አንተ ያምጡት፥ ታናሹንም ነገር ሁሉ እነርሱ ይፍረዱ፤ እነርሱም ከአንተ ጋር ሸክሙን ይሸከማሉ፥ ለአንተም ይቀልልልሃል። 23ይህንም ብታደርግ፥ እግዚአብሔር እንዲሁ ቢያዝዝህ፥ መቆም ይቻልሃል፥ ደግሞም ይህ ሕዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል። 24ሙሴም የአማቱን ቃል ሰማ፥ ያለውንም ሁሉ አደረገ። 25ሙሴም ከእስራኤል ሁሉ አዋቂዎችን መረጠ፥ በሕዝቡም ላይ የሺህ አለቆች፥ የመቶም አለቆች፥ የአምሳም አለቆች፥ የአሥርም አለቆች አድርጎ ሾማቸው። 26በሕዝቡም ላይ ሁልጊዜ ፈረዱ፤ የከበደባቸውንም ነገር ወደ ሙሴ አመጡ፥ ታናሹን ነገር ሁሉ ግን እነርሱ ፈረዱ። 27ሙሴም አማቱን ሰደደው፤ እርሱም ወደ አገሩ ተመለሰ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in