YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘጸአት 15

15
የሙሴ መዝሙር
1በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፤ እንዲህም ብለው ተናገሩ፤ “በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ።
2ጉልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፤
መድኃኒቴም ሆነልኝ፤
ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ፤ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ።
3እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው፤
4የፈርዖንን ሰረገሎች ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው፤
የተመረጡት ሦስተኞች በኤርትራ ባሕር ሰጠሙ።
5ቀላያትም ከደኑአቸው፤
ወደ ባሕር ጥልቀት እንደ ድንጋይ ሰጠሙ።
6አቤቱ፥ ቀኝህ በኃይል ከበረ፤
አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቱን አደቀቀ።
7በክብርህም ብዛት የተነሡብህን አጠፋህ፤
ቍጣህን ሰድደህ፤ እንደ ገለባም በላቸው።
8በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ፤
ፈሳሾቹም እንደ ክምር ቆሙ፤
ሞገዱም በባሕር ውስጥ ረጋ።
9ጠላትም፥ ‘አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፤
ምርኮም እካፈላለሁ፤ ነፍሴም ትጠግባቸዋለች፤
ሰይፌንም እመዝዛለሁ፤ እጄም ታጠፋቸዋለች’ አለ።
10ነፋስህን አነፈስህ፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ አረር ሰጠሙ።
11አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? 12ቀኝህን ዘረጋህ፥ ምድርም ዋጠቻቸው። 13በቸርነትህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራህ፤ በኃይልህ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ አገባሃቸው። 14አሕዛብ ሰሙ፥ ተንቀጠቀጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ምጥ ያዛቸው። 15የዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ደነገጡ፤ የሞአብን ኃያላን መንቀጥቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ። 16አቤቱ፥ ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ፥ የተቤዠኸው ሕዝብ እስኪያልፍ ድረስ፥ ፍርሃትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፤ በክንድህ ብርታት እንደ ድንጋይ ዝም አሉ። 17አቤቱ፥ አንተ ታስገባቸዋለህ፥ በርስትህ ተራራም ትተክላቸዋለህ፥ አቤቱ፥ ለማደሪያህ ባደረግኸው ስፍራ፥ አቤቱ፥ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ። 18እግዚአብሔር ለዘላለሙ እስከ ፍጻሜ ይነግሣል። 19የፈርዖን ፈረሶች ከሰረገሎቹ ከፈረሰኞቹም ጋር ወደ ባሕር ገቡ፥ እግዚአብሔርም የባሕሩን ውኆች መለሰባቸው፤ የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ መካከል በየብስ ሄዱ። 20የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዘፈን በኋላዋ ወጡ። 21ማርያምም እየዘመረች መለሰችላቸው፦ በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። 22ሙሴም እስራኤልን ከኤርትራ ባሕር አስጓዘ፥ ወደ ሱርም ምድረ በዳ ወጡ፤ በምድረ በዳም ሦስት ቀን ሄዱ፥ ውኃም አላገኙም። 23ወደ ማራም በመጡ ጊዜ የማራ ውኃ መራራ ነበረና ሊጠጡ አልቻሉም፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም ማራ ተብሎ ተጠራ። 24ሕዝቡም፦ ምን እንጠጣለን? ብለው በሙሴ ላይ አንጎራጎሩ። 25ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም እንጨትን አሳየው፥ በውኃውም ላይ ጣለው፥ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዓትንና ፍርድን አደረገላቸው፥ በዚያም ፈተናቸው፤ 26እርሱም፦ አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ፥ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና አለ። 27እነርሱም ወደ ኤሊም መጡ፥ በዚያም አሥራ ሁለት የውኃ ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ነበሩባት፤ በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in