ትንቢተ አሞጽ 1
1
1በቴቁሔ ከላም ጠባቂዎች መካከል የነበረ አሞጽ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን፥ በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን፥ የምድር መናወጥ ከሆነበቱ ከሁለት ዓመት በፊት ስለ እስራኤል ያየው ቃል ይህ ነው።
2እንዲህም አለ፦ እግዚአብሔር በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፥ የእረኞችም ማሰማርያዎች ያለቅሳሉ፥ የቀርሜሎስም ራስ ይደርቃል።
3እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ገለዓድን በብረት መንኰራኵር አሂዶአልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የደማስቆ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። 4በአዛሄል ቤት እሳትን እሰድዳለሁ፥ የወልደ አዴርንም አዳራሾች ትበላለች። 5የደማስቆንም መወርወሪያ እሰብራለሁ፥ ተቀማጮችንም ከአዌን ሸለቆ አጠፋለሁ፥ በትር የያዘውንም ከዔደን ቤት አጠፋለሁ፥ የሶርያም ሕዝብ ወደ ቂር ይማርካል፥ ይላል እግዚአብሔር።
6እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለኤዶምያስ አሳልፈው ይሰጡአቸው ዘንድ ምርኮኞችን ሁሉ ማርከዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጋዛ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። 7በጋዛ ቅጥር ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችዋንም ትበላለች። 8ተቀማጮችን ከአዛጦን አጠፋለሁ፥ በትር የያዘውንም ከአስቀሎና አጠፋለሁ፥ እጄንም በአቃሮን ላይ እመልሳለሁ፥ ከፍልስጥኤማውያንም የቀሩት ይጠፋሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
9እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ምርኮኞችን ሁሉ ለኤዶምያስ አሳልፈው ሰጥተዋልና፥ የወንድሞችንም ቃል ኪዳን አላሰቡምና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጢሮስ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። 10በጢሮስ ቅጥር ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችዋንም ትበላለች።
11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወንድሙን በሰይፍ አሳድዶታልና፥ ርኅራኄንም ሁሉ ጥሎአልና፥ ቍጣውም ሁልጊዜ ቀድዶአልና፥ መዓቱንም ለዘላለም ጠብቆአልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የኤዶምያስ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። 12በቴማን ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ የባሶራንም አዳራሾች ትበላለች።
13እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዳርቻቸውን ያሰፉ ዘንድ የገለዓድን እርጕዞች ቀድደዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የአሞን ልጆች ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። 14በረባት ቅጥር ላይ እሳትን አነድዳለሁ፥ በሰልፍም ቀን በጩኸት በዐውሎ ነፋስም ቀን በሁከት አዳራሾችዋን ትበላለች፥ 15ንጉሣቸውም ከአለቆቹ ጋር በአንድነት ይማረካል፥ ይላል እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ አሞጽ 1: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in