YouVersion Logo
Search Icon

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 22

22
አካዝያስ በይሁዳ ላይ እንደነገሠ
(2ነገ. 8፥25-299፥21-29)
1በኢየሩሳሌም የነበሩትም ታናሹን ልጁን አካዝያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡት። የመጣባቸው የዓረብና የአሊማዞን የሽፍቶች ጭፍራ የእርሱን ታላቆች ገድለዋቸው ነበርና። የይሁዳም ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ነገሠ። 2አካዝያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው አርባ ሁለት ዓመት ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ጎቶሊያ የተባለች የዖምሪ ልጅ ነበረች። 3እናቱም ክፉ ለማድረግ ትመክረው ነበርና እርሱ ደግሞ በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ። 4አባቱም ከሞተ በኋላ የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ እስኪጠፉ ድረስ መካሪዎች ነበሩትና። 5በምክራቸውም ሄደ፤ ከእስራኤልም ንጉሥ ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን በሬማት ዘገለአድ ሊዋጋ ሄደ፤ ሶርያውያንም ኢዮራንም አቈሰሉት። 6ከሶርያም ንጉሥ ከአዛኤል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን በሬማት ያቈሰሉትን ቍስል ይታከም ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ፤ ታምሞም ነበርና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ የአክዓብን ልጅ ኢዮራምን ያይ ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።
7አካዝያስም ወደ ኢዮራም በመምጣቱ ይጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበረ፤ በመጣም ጊዜ ከኢዮራም ጋር እግዚአብሔር የአክዓብን ቤት ያጠፋ ዘንድ ወደ ቀባው ወደ ናሜሲ ልጅ ወደ ኢዩ ወጣ። 8ኢዩም በአክዓብ ቤት ላይ ፍርድን ሲፈጽም የይሁዳን መሳፍንትና አካዝያስን ያገለግሉ የነበሩትን የአካዝያስን ወንድሞች ልጆች አግኝቶ ገደላቸው። 9አካዝያስንም ፈልገው፤ በሰማርያም ተሸሽጎ ሳለ አገኙት፤ ወደኢዩም አምጥተው ገደሉትና “በፍጹም ልብ እግዚአብሔርን የፈለገው የኢዮሳፍጥ ልጅ ነው” ብለው ቀበሩት። ከአካዝያስም ቤት ማንም መንግሥትን ይይዝ ዘንድ የሚችል አልነበረም።
ጎቶልያ በይሁዳ እንደነገሠች (2ነገ. 11፥1-3)
10የአካዝያስም እናት ጎቶሊያ ልጅዋ እንደ ሞተ ባየች ጊዜ ተነሥታ የይሁዳን ቤተ መንግሥት ዘር ሁሉ አጠፋች። 11የንጉሡ ልጅ ዮሳቤት ግን ከተገደሉት ከንጉሡ ልጆች መካከል የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ሰርቃ ወሰደች፤ እርሱንና ሞግዚቱን በእልፍኝ ውስጥ አኖረቻቸው፤ ጎቶሊያ እንዳታስገድለው የንጉሡ የኢዮራም ልጅ የአካዝያስ እኅት የካህኑ የዮዳሄ ሚስት ዮሳቤት እንዲሁ ሸሸገችው። 12በእነርሱም ዘንድ ተሸሽጎ በእግዚአብሔር ቤት ስድስት ዓመት ያህል ተቀመጠ፤ ጎቶልያም በምድር ላይ ነገሠች።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Videos for ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 22