ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 17
17
ኢዮሳፍጥ በይሁዳ ላይ እንደነገሠ (1ነገ.15፥24)
1በእርሱ ፋንታ ልጁ ኢዮሳፍጥ ነገሠ፤ በእስራኤልም ላይ ጠነከረ። 2በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ወታደሮችን አኖረ፤ በይሁዳም አገር አባቱም አሳ በወሰዳቸው በኤፍሬም ከተሞች ዘበኞችን አስቀመጠ። 3እግዚአብሔርም ከኢዮሳፍጥ ጋር ነበረ፤ በፊተኛይቱ በአባቱ በዳዊት መንገድ ሄዶአልና፤ በኣሊምንም አልፈለገምና፤ 4ነገር ግን የአባቱን አምላክ ፈለገ፤ በትእዛዙም ሄደ፤ የእስራኤልንም ሥራ አልሠራም። 5እግዚአብሔርም መንግሥቱን በእጁ አጸና፤ ይሁዳም ሁሉ እጅ መንሻ ለኢዮሳፍጥ አመጣ፤ እጅግም ብዙ ብልጥግናና ክብር ሆነለት። 6ልቡም በእግዚአብሔር መንገድ ከፍ ከፍ አለ፤ የኮረብታውን መስገጃዎችና የማምለኪያ ዐፀዱንም ከይሁዳ አስወገደ።
7በነገሠም በሦስተኛው ዓመት በይሁዳ ከተሞች ያስተምሩ ዘንድ መሳፍንቱን፥ ቤንኃይልን፥ አብድያስን፥ ዘካርያስን፥ ናትናኤልንና ሚክያስን ሰደደ። 8ከእነርሱም ጋር ሌዋውያንን፥ ሸማያን፥ ነታንያን፥ ዝባድያን፥ አሣሄልን፥ ሰሚራሞትን፥ ዮናትንን፥ አዶንያስን፥ ጦብያንና ጦባዶንያን ሰደደ፤ ከእነርሱም ጋር ካህናቱን ኤሊሳማንና ኢዮራምን ሰደደ። 9እነርሱም የእግዚአብሔርን የሕጉን መጽሐፍ ይዘው በይሁዳ ያስተምሩ ነበር፤ ወደ ይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሄደው ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር።
10በይሁዳም ዙሪያ በነበሩ መንግሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ድንጋጤ ሆነ፤ ከኢዮሳፍጥም ጋር አልተዋጉም። 11ከፍልስጥኤማውያንም ለኢዮሳፍጥ እጅ መንሻና የብር ግብር ያመጡ ነበሩ፤ ዓረባውያንም ደግሞ ከመንጎቻቸው ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ በጎችና ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ ፍየሎች ያመጡለት ነበር። 12ኢዮሳፍጥም እየበረታና እጅግም እየከበረ ሄደ፤ በይሁዳም ግንቦችንና የጎተራ ከተሞችን ሠራ። 13በይሁዳም ከተሞች ብዙ ሥራ ሠራ፤ በኢየሩሳሌምም ጽኑዓን ኃያላን ሰልፈኞች ነበሩት። 14ቍጥራቸውም እንደ አባቶቻቸው ቤት ይህ ነበረ፤ ከይሁዳ ሻለቆች አለቃው ዓድና፥ ከእርሱም ጋር ሦስት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ፤ 15ከእርሱም በኋላ አለቃው ይሆሐናን፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ 16ከእርሱም በኋላ በፈቃዱ ራሱን ለእግዚአብሔር የቀደሰ የዝክሪ ልጅ ዓማስያ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ። 17ከብንያምም ጽኑዕ ኃያል የነበረው ኤሊዳሄ፥ ከእርሱም ጋር ቀስትና ጋሻ የሚይዙ ሁለት መቶ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ 18ከእርሱም በኋላ ዩዛባት፥ ከእርሱም ጋር ለሰልፍ የተዘጋጁ መቶ ሰማኒያ ሺህ ሰዎች ነበሩ። 19ንጉሡ በተመሸጉ በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ካኖራቸውም ሌላ እነዚህ ንጉሡን ያገለግሉ ነበር።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 17: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in