አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7
7
1የቂርያትይዓሪም ሰዎችም መጥተው የእግዚአብሔርን ታቦት አወጡ፥ በኮረብታውም ላይ ወዳለው ወደ አሚናዳብ ቤት አገቡት፥ የእግዚአብሔርንም ታቦት እንዲጠብቅ ልጁን አልዓዛርን ቀደሱት። 2ታቦቱም በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠበት ቀን ጀምሮ ወራቱ ረዘመ፥ ሀያ ዓመትም ሆነ፥ የእስራኤልም ቤት ሁሉ አዝኖ እግዚአብሔርን ተከተለ።
3ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ፦ በሙሉ ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሳችሁ እንግዶችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እግዚአብሔር አቅኑ፥ እርሱንም ብቻ አምልኩ፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ያድናችኋል ብሎ ተናገራቸው። 4የእስራኤልም ልጆች በኣሊምንና አስታሮትን አራቁ፥ እግዚአብሔርንም ብቻ አመለኩ።
5ሳሙኤልም፦ እስራኤልን ሁሉ ወደ ምጽጳ ሰበስቡ፥ ስለ እናንተም ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ አለ። 6ወደ ምጽጵም ተሰበሰቡ፥ ውኃም ቀድተው በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሱ፥ በዚያም ቀን ጾሙ፥ በዚያም፦ እግዚአብሔርን በድለናል አሉ። ሳሙኤልም በእስራኤል ልጆች ላይ በምጽጳ ፈረደ። 7ፍልስጥኤማውያንም የእስራኤል ልጆች ወደ ምጽጳ እንደ ተሰበሰቡ በሰሙ ጊዜ የፍልስጥኤማውያን አለቆች በእስራኤል ላይ ወጡ፥ የእስራኤልም ልጆች ሰምተው ፍልስጥኤማውያንን ፈሩ። 8የእስራኤልም ልጆች ሳሙኤልን፦ ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድነን ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ትጸልይልን ዘንድ አትታክት አሉት። 9ሳሙኤልም አንድ የሚጠባ የበግ ጠቦት ወስዶ ለእግዚአብሔር ፈጽሞ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው፥ ሳሙኤልም ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ጮኽ፥ እግዚአብሔርም ሰማው። 10ሳሙኤልም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሲያሳርግ ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል ጋር ሊዋጉ ቀረቡ፥ እግዚአብሔርም በዚያች ቀን በፍልስጥኤማውያን ላይ ታላቅ ነጎድጓድ አንጎደጎደ፥ አስደነገጣቸውም፥ በእስራኤልም ፊት ድል ተመቱ። 11የእስራኤልም ሰዎች ከምጽጳ ወጡ፥ ፍልስጥኤማውያንንም አሳደዱ፥ በቤትካር ታችም እስኪደርሱ ድረስ መቱአቸው።
12ሳሙኤልም አንድ ድንጋይ ወስዶ በምጽጳና በሼን መካከል አኖረው፥ ስሙንም፦ እስከ አሁን ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል ሲል አቤንኤዘር ብሎ ጠራው። 13ፍልስጥኤማውያንም ተዋረዱ፥ ዳግመኛም ከዚያ ወዲያ ወደ እስራኤል ድንበር አልወጡም፥ በሳሙኤል ዕድሜ ሁሉ የእግዚአብሔር እጅ በፍልስጥኤማውያን ላይ ነበረች። 14ፍልስጥኤማውያንም ከአስቀሎና ጀምሮ እስከ ጌት ድረስ ከእስራኤል የወሰዱአቸው ከተሞች ለእስራኤል ተመለሱ፥ እስራኤልም ድንበሩን ከፍልስጥኤማውያን እጅ አዳነ። በእስራኤልና በአሞራውያንም መካከል ዕርቅ ነበረ።
15ሳሙኤልም በዕድሜው ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። 16በየዓመቱም ወደ ቤቴል ወደ ጌልገላ ወደ ምጽጳም ይዞር ነበር፥ በእነዚያም ስፍራዎች ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። 17ቤቱም በዚያ ነበረና ወደ አርማቴም ይመለስ ነበር፥ በዚያም በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር፥ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in