አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19
19
1ሳኦልም ለልጁ ለዮናታንና ለባሪያዎቹ ሁሉ ዳዊትን ይገድሉ ዘንድ ነገራቸው። የሳኦል ልጅ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድድ ነበር። 2ዮናታንም፦ አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ፈልጎአል፥ አሁን እንግዲህ ለነገው ተጠንቅቀህ ተሸሸግ፥ በስውርም ተቀመጥ፥ 3እኔም እወጣለሁ አንተም ባለህበት እርሻ በአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፥ ስለ አንተም ከአባቴ ጋር እነጋገራለሁ፥ የሆነውንም አይቼ እነግርሃለሁ ብሎ ለዳዊት ነገረው። 4ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል፦ እርሱ አልበደለህምና፥ ሥራውም ለአንተ እጅግ መልካም ሆኖአልና ንጉሡ ባሪያውን ዳዊትን አይበድለው፥ 5ነፍሱንም በእጁ ጥሎ ፍልስጥኤማዊውን ገደለ፥ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ሁሉ ታላቅ መድኃኒት አደረገ፥ አንተም አይተህ ደስ አለህ፥ በከንቱ ዳዊትን በመግደልህ ስለ ምን በንጹሕ ደም ላይ ትበድላለህ? ብሎ ስለ ዳዊት መልካም ተናገረ።
6ሳኦልም የዮናታንን ቃል ሰማ፥ ሳኦልም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም ብሎ ማለ። 7ዮናታንም ዳዊትን ጠርቶ ይህን ነገር ሁሉ ነገረው፥ ዮናታንም ዳዊትን ወደ ሳኦል አመጣው፥ እንደ ቀድሞውም በፊቱ ነበረ።
8ዳግሞም ጦርነት ሆነ፥ ዳዊትም ወጥቶ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፥ ታላቅ ግዳይም ገደላቸው፥ ከፊቱም ሸሹ። 9ሳኦልም ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው። ዳዊትም በእጁ በገና ይመታ ነበር። 10ሳኦልም ዳዊትን ከግንብ ጋር ያጣብቀው ዘንድ ጦሩን ወረወረ፥ ዳዊትም ከሳኦል ፊት ዘወር አለ፥ ጦሩም በግንቡ ውስጥ ተተከለ፥ በዚያም ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ። 11ሳኦልም ዳዊትን ጠብቀው በነጋው እንዲገድሉት መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ቤት ላከ፥ ሚስቱም ሜልኮል፦ በዚህች ሌሊት ነፍስህን ካላዳንህ ነገ ትገደላለህ ብላ ነገረችው። 12ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አወረደችው፥ ሄደም፥ ሸሽቶም አመለጠ። 13ሜልኮልም ተራፊምን ወስዳ በአልጋ ላይ አኖረችው፥ በራስጌውም ጉንጉን የፍየል ጠጉር አደረገች፥ በልብስም ከደነችው። 14ሳኦልም ዳዊትን እንዲያመጡት መልእክተኞችን ላከ፥ እርስዋም፦ ታምሞአል አለቻቸው። 15ሳኦልም፦ እገድለው ዘንድ ዳዊትን ከነ አልጋው አምጡልኝ ብሎ መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ሰደደ። 16መልእክተኞቹም በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ተራፊሙን በአልጋው ላይ አገኙ፥ በራስጌው ጕንጕን የፍየል ጠጉር ነበረ። 17ሳኦልም ሜልኮልን፦ ስለ ምን እንዲህ አድርገሽ አታለልሽኝ? ጠላቴን አስኮበለልሽው አላት። ሜልኮልም ለሳኦል፦ እርሱ፦ አውጥተሽ ስደጂኝ፥ አለዚያም እገድልሻለሁ አለኝ ብላ መለሰችለት።
18ዳዊትም ሸሽቶ አመለጠ፥ ወደ አርማቴምም ወደ ሳሙኤል መጣ፥ ሳኦልም ያደረገበትን ሁሉ ነገረው፥ እርሱና ሳሙኤልም ሄዱ በነዋትዘራማም ተቀመጡ። 19ሳኦልም፦ ዳዊት፥ እነሆ፥ በአርማቴም አገር በነዋትዘራማ ተቀምጦአል የሚል ወሬ ሰማ። 20ሳኦልም ዳዊትን ያመጡት ዘንድ መልእክተኞችን ሰደደ፥ የነቢያት ጉባኤ ትንቢት ሲናገሩ፥ ሳሙኤልም አለቃቸው ሆኖ ሲቆም ባዩ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል መልእክተኞች ላይ ወረደ፥ እነርሱም ትንቢት ይናገሩ ጀምር። 21ሳኦልም ያንን በሰማ ጊዜ ሌሎች መልእክተኞችን ሰደደ፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። ሳኦልም እንደ ገና ሦስተኛ ጊዜ መልእክተኞችን ሰደደ፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። 22የሳኦልም ቁጣ ነደደ፥ እርሱም ደግሞ ወደ አርማቴም መጣ፥ በሤኩም ወዳለው ወደ ታላቁ የውኃ ጕድጓድ ደረሰ። ሳሙኤልና ዳዊት የት ናቸው? ብሎ ጠየቀ፥ አንድ ሰውም፦ እነሆ፥ በአርማቴም አገር በነዋትዘራማ ናቸው አለው። 23ወደ አርማቴምም አገር ወደ ነዋትዘራማ ሄደ፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ደግሞ ወረደ፥ እርሱም ሄደ፥ ወደ አርማቴምም አገር ወደ ነዋትዘራማ እስኪመጣ ድረስ ትንቢት ይናገር ነበር። 24ልብሱንም አወለቀ፥ በሳሙኤልም ፊት ትንቢት ተናገረ፥ ራቁቱንም ወድቆ በዚያ ቀን ሁሉ በዚያም ሌሊት ሁሉ ተጋደመ። ስለዚህ፦ ሳኦል ደግሞ ከነቢያት መካከል ነውን? ይባባሉ ነበር።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in