አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17
17
1ፍልስጥኤማውያንም ጭፍሮቻቸውን በይሁዳ ባለው በሰኮት አከማቹ፥ በሰኮትና በዓዜቃ መካከል በአርፌስደሚም ሰፈሩ። 2ሳኦልና የእስራኤል ሰዎች ተከማቹ፥ በዔላ ሸለቆም ሰፈሩ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ሊዋጉ ተሰለፉ። 3ፍልስጥኤማውያንም በአንድ ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፥ እስራኤልም በሌላው ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፥ በመካከላቸውም ሸለቆ ነበረ። 4ከፍልስጥኤማውያንም ሰፈር የጌት ሰው ጎልያድ፥ ቁመቱም ስድስት ክንድ ከስንዝር የሆነ፥ ዋነኛ ጀግና መጣ። 5በራሱም የናስ ቁር ደፍቶ ነበር፥ ጥሩርም ለብሶ ነበር፥ የጥሩሩም ሚዛን አምስት ሺህ ሰቅል ናስ ነበረ። 6በእግሮቹም ላይ የናስ ገምባሌ ነበረ፥ የናስም ጭሬ በትከሻው ላይ ነበረ። 7የጦሩም የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅልያ ነበረ፥ የጦሩም ሚዛን ስድስት መቶ ሰቅል ብረት ነበረ፥ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። 8እርሱም ቆሞ ወደ እስራኤል ጭፍሮች ጮኸ፦ ለሰልፍ ትሠሩ ዘንድ ለምን ወጣችሁ? እኔ ፍልስጥኤማዊ፥ እናንተም የሳኦል ባሪያዎች አይደላችሁምን? ለእናንተ አንድ ሰው ምረጡ፥ ወደ እኔም ይውረድ፥ 9ከእኔም ጋር ሊዋጋ ቢችል ቢገድለኝም፥ ባሪያዎች እንሆናችኋለን፥ እኔ ግን ባሸንፈው ብገድለውም፥ እናንተ ባሪያዎች ትሆኑናላችሁ፥ ለእኛም ትገዛላችሁ አለ። 10ፍልስጥኤማዊውም፦ ዛሬ የእስራኤልን ጭፎሮች ተገዳደርኋቸው፥ እንዋጋ ዘንድ አንድ ሰው ስጡኝ አለ። 11ሳኦልና እስራኤልም ሁሉ እንዲህ የሚላቸውን የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፥ ደነገጡም።
12ዳዊትም የዚያ የኤፍራታዊው ሰው ልጅ ነበረ፥ ያም ሰው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ስሙም እሴይ ነበረ፥ ስምንትም ልጆች ነበሩት፥ በሳኦልም ዘመን በዕድሜ አርጅቶ ሸምግሎም ነበር። 13የእሴይም ሦስቱ ታላላቆች ልጆቹ ሳኦልን ተከትለው ወደ ሰልፉ ሄደው ነበር፥ ወደ ሰልፉም የሄዱት የሦስቱ ልጆቹ ስም ይህ ነበረ፥ ታላቁ ኤልያብ ሁለተኛውም አሚናዳብ ሦስተኛውም ሣማ ነበረ። 14ዳዊት የሁሉ ታናሽ ነበረ፥ ሦስቱም ታላላቆች ሳኦልን ተከትለው ነበር። 15ዳዊትም የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተ ልሔም ይመላለስ ነበር። 16ፍልስጥኤማዊውም ጥዋትና ማታ ይቀርብ፥ አርባ ቀንም ይታይ ነበር።
17እሴይም ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ ከዚህ ከተጠበሰው እሸት አንድ የኢፍ መስፈሪያ እነዚህንም አሥር እንጀራዎች ለወንድሞችህ ውሰድ፥ ወደ ሰፈሩም ወደ ወንድሞችህ ፈጥነህ አድርሳቸው፥ 18ይህንም አሥሩን አይብ ወደ ሻለቃው ውሰደው፥ የወንድሞችህንም ደኅንነት ጠይቅ፥ ወሬአቸውንም አምጣልኝ። 19ሳኦልና እነርሱ የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ በዔላ ሸለቆ ነበሩ። 20ዳዊትም ማልዶ ተነሣ፥ በጎቹንም ለጠባቂ ተወ፥ እሴይም ያዘዘውን ይዞ ሄደ፥ ጭፍራውም ተሰልፎ ሲወጣ ለሰልፍም ሲጮኽ በሰረገሎች ወደ ተከበበው ሰፈር መጣ። 21እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ፊት ለፊት ተሰላልፈው ነበረ። 22ዳዊትም ዕቃውን በዕቃ ጠባቂው እጅ አኖረው፥ ወደ ሠራዊቱም ሮጠ፥ የወንድሞቹንም ደኅንነት ጠየቀ። 23እርሱም ሲነጋገራቸው፥ እነሆ፥ ጎልያድ የተባለው ያ ዋነኛ ጀግና ፍልስጥኤማዊ የጌት ሰው ከፍልስጥኤማውያን ጭፍራ መካከል ወጣ፥ የተናገረውንም ቃል ተናገረ፥ ዳዊትም ሰማ። 24የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ሰውዮውን ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው ከእርሱ ሸሹ። 25የእስራኤልም ሰዎች፦ ይህን የወጣውን ሰው አያችሁትን? በእውነት እስራኤልን ሊገዳደር ወጣ፥ የሚገድለውንም ሰው ንጉሡ እጅግ ባለጠጋ ያደርገዋል፥ ልጁንም ይድርለታል፥ ያባቱንም ቤተ ሰብ በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያወጣቸዋል አሉ። 26ዳዊትም በአጠገቡ ለቆሙት ሰዎች፦ ይህን ፍልስጥኤማዊ ለሚገድል፥ ከእስራኤልም ተግዳሮትን ለሚያርቅ ሰው ምን ይደረግለታል? የሕያውን አምላክ ጭፍሮች የሚገዳደር ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው። 27ሕዝቡም፦ ለሚገድለው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ብለው እንደ ቀድሞው መለሱለት።
28ታላቅ ወንድሙም ኤልያብ ከሰዎች ጋር ሲነጋገር ሰማ፥ የኤልያብም ቁጣ በዳዊት ላይ ነድዶ፦ ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂቶች በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? እኔ ኩራትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁና ሰልፉን ለማየት መጥተሃል አለው። 29ዳዊትም፦ እኔ ምን አደረግሁ? ይህ ታላቅ ነገር አይደለምን? አለ። 30ዳዊትም ከእርሱ ወደ ሌላ ሰው ዘወር አለ፥ እንደዚህም ያለ ነገር ተናገረ፥ ሕዝቡም እንደ ቀድሞው ያለ ነገር መለሱለት።
31ዳዊትም የተናገረው ቃል ተሰማ፥ ለሳኦልም ነገሩት፥ ወደ እርሱም አስጠራው። 32ዳዊትም ሳኦልን፦ ስለ እርሱ የማንም ልብ አይውደቅ፥ እኔ ባሪያህ ሄጄ ያንን ፍልስጥኤማዊ እወጋዋለሁ አለው። 33ሳኦልም ዳዊትን፦ አንተ ገና ብላቴና ነህና፥ እርሱም ከብላቴንነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነውና ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም አለው። 34ዳዊትም ሳኦልን አለው፦ እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳና ድብ ይመጣ ነበር፥ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር። 35በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፥ ከአፉም አስጥለው ነበር፥ በተነሣብኝም ጊዜ ጉሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበር። 36እኔ ባሪያህ አንበሳና ድብ መታሁ፥ ይህም ያልተገረዘው ፍልስጥኤማዊ የሕያውን አምላክ ጭፍሮች ተገዳድሮአልና ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። 37ዳዊትም፦ ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል አለ። ሳኦልም ዳዊትን፦ ሂድ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል አለው። 38ሳኦልም ዳዊትን የገዛ ራሱን ልብስ አለበሰው፥ በራሱም ላይ የናስ ቁር ደፋለት፥ ጥሩርም አለበሰው። 39ዳዊትም ሰይፉን በልብሱ ላይ ታጠቀ፥ ገናም አልፈተነውምና መሄድ ሞከረ። ዳዊትም ሳኦልን፦ አልፈተንሁትምና እንዲህ ብዬ መሄድ አልችልም አለው። ዳዊትም አወለቀ። 40በትሩንም በእጁ ወሰደ፥ ከወንዝም አምስት ድብልብል ድንጋዮችን መረጠ፥ በእረኛ ኮረጆውም በኪሱ ከተታቸው፥ ወንጭፍም በእጁ ነበረ፥ ወደ ፍልስጥኤማዊውም ቀረበ።
41ፍልስጥኤማዊውም መጥቶ ወደ ዳዊት ቀረበ፥ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። 42ጎልያድም ዳዊትን ትኩር ብሎ አየው፥ ቀይ ብላቴና መልኩም ያማረ ነበረና ናቀው። 43ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፦ በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን? አለው። ፍልስጥኤማዊውም በአምላኮቹ ስም ዳዊትን ረገመው። 44ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፦ ወደ እኔ ና፥ ሥጋህንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ አለው። 45ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን አለው፦ አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፥ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። 46እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፥ እመታህማለሁ፥ ራስህንም ከአንተ አነሣዋለሁ፥ የፍልስጥኤማውያንንም ሠራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ዛሬ እሰጣለሁ። ይኸውም ምድር ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ታውቅ ዘንድ፥ 47ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደል ያውቅ ዘንድ ነው። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፥ እናንተንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል። 48ፍልስጥኤማዊውም ተነሥቶ ዳዊትን ሊገናኘው በቀረበ ጊዜ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ሊገናኘው ወደ ሰልፉ ሮጠ።
49ዳዊትም እጁን ወደ ኮረጆው አግብቶ አንድ ድንጋይ ወሰደ፥ ወነጨፈውም፥ ፍልስጥኤማዊውንም ግምባሩን መታ፥ ድንጋዩም በግምባሩ ተቀረቀረ፥ እርሱም በምድር ላይ በፊቱ ተደፋ።
50ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው፥ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለ፥ በዳዊትም እጅ ሰይፍ አልነበረም። 51ዳዊትም ሮጦ በፍልስጥኤማዊው ላይ ቆመ፥ ሰይፉንም ይዞ ከሰገባው መዘዘው፥ ገደለውም፥ ራሱንም ቆረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ዋናቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ሸሹ። 52የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ተነሥተው እልል አሉ፥ ፍልስጥኤማውያንንም እስከ ጌትና እስከ አስቀሎና በር ድረስ አሳደዱአቸው። ፍልስጥኤማውያንም ከሸዓራይም ጀምሮ እስከ ጌትና እስከ አቃሮን ድረስ በመንገድ ላይ የተመቱት ወደቁ። 53የእስራኤልም ልጆች ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመልሰው ሰፈራችውን በዘበዙ። 54ዳዊትም የፍልስጥኤማዊውን ራስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፥ ጋሻ ጦሩን ግን በድንኳኑ ውስጥ አኖረው።
55ሳኦልም ዳዊትን ወደ ፍልስጥኤማዊው ሲወጣ ባየው ጊዜ ለሠራዊቱ አለቃ ለአበኔር፦ አበኔር ሆይ፥ ይህ ብላቴና የማን ልጅ ነው? አለው። አበኔርም፦ ንጉሥ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፥ አላውቅም አለ። 56ንጉሡም፦ ይህ ብላቴና የማን ልጅ እንደ ሆነ አንተ ጠይቅ አለ። 57ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ አበኔር ወሰደው፥ ወደ ሳኦልም ፊት አመጣው፥ የፍልስጥኤማዊውንም ራስ በእጁ ይዞ ነበር። 58ሳኦልም፦ አንተ ብላቴና፥ የማን ልጅ ነህ? አለው። ዳዊትም፦ እኔ የቤተ ልሔሙ የባሪያህ የእሴይ ልጅ ነኝ ብሎ መለሰ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in