ትንቢተ ዘካርያስ 6
6
1ተመልሼም ዓይኖቼን አነሣሁ፥ እነሆም፥ አራት ሰረገሎች ከሁለት ተራራ መካከል ሲወጡ አየሁ፣ ተራሮቹም የናስ ተራሮች ነበሩ። 2በፊተኛው ሰረገላ መጋላ ፈረሶች፥ በሁለተኛውም ሰረገላ ዱሪ ፈረሶች ነበሩ፥ 3በሦስተኛውም ሰረገላ አምባላይ ፈረሶች፥ በአራተኛውም ሰረገላ ቅጥልጣል ፈረሶች ነበሩ። 4ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረውም መልአክ መልሼ፦ ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁት። 5መልአኩም መልሶ፦ እነዚህ በምድር ሁሉ ጌታ ፊት ከቆሙበት ስፍራ የሚወጡ አራቱ የሰማይ ነፋስት ናቸው። 6ዱሪ ፈረሶች ያሉበት ወደ ሰሜን ይወጣል፣ አምባላዮቹም ከእነርሱ በኋላ ይወጣሉ፥ ቅጥልጣሎቹም ወደ ደቡብ ይወጣሉ አለኝ። 7መጋላዎቹም ደግሞ ወጡ በምድርም ይመላለሱ ዘንድ ለመሄድ ይፈልጉ ነበር፣ እርሱም፦ ሂዱ፥ በምድር ላይ ተመላለሱ አለ። እነርሱም በምድር ላይ ተመላለሱ። 8ጮኾም፦ እነሆ፥ ወደ ሰሜን ምድር የሚወጡት እነርሱ መንፈሴን በሰሜን ምድር ላይ አሳርፈዋል ብሎ ተናገረኝ።
9የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 10ከባቢሎን ከመጡት ምርኮኞች ከሔልዳይና ከጦብያ ከዮዳኤም ውሰድ፣ በዚያም ቀን መጥተህ ወደ ሶፎንያስ ልጅ ወደ ኢዮስያስ ቤት ግባ። 11ብርንና ወርቅን ከእነርሱ ውሰድ፥ አክሊሎችንም ሥራ፣ በታላቁም ካህን በኢዮሴዴቅ ልጅ በኢያሱ ራስ ላይ ድፋቸው፥ እንዲህም በለው፦ 12የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ስሙ ቍጥቋጥ የሚባል ሰው በስፍራው ይበቅላል፥ የእግዚአብሔርንም መቅደስ ይሠራል። 13እርሱ የእግዚአብሔርን መቅደስ ይሠራል፥ ክብርንም ይሸከማል፥ በዙፋኑም ላይ ተቀምጦ ይነግሣል፣ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል፥ የሰላምም ምክር በሁለቱ መካከል ይሆናል። 14አክሊሎችም ለሔሌምና ለጦብያ ለዮዳኤም ለሶፎንያስም ልጅ ለሔን በእግዚአብሔር መቅደስ ውስጥ ለመታሰቢያ ይሆናሉ። 15በሩቅም ያሉት መጥተው የእግዚአብሔርን መቅደስ ይሠራሉ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቃችሁ ብትሰሙ ይህ ይሆናል።
Currently Selected:
ትንቢተ ዘካርያስ 6: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in