ወደ ሮሜ ሰዎች 1
1
ስለ መጠራቱ
1የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማስተማር ተለይቶ ከተጠራ ሐዋርያ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ከሚሆን ከጳውሎስ፥ 2በነቢያቱ ቃልና በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ በተስፋ ያናገረው፥ 3ከዳዊት ዘር ሰው ሆኖ በሥጋ ስለ ተወለደ ስለ ልጁ፥ 4የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በኀይሉና በመንፈስ ቅዱስ፥ ከሙታንም ተለይቶ በመነሣቱ ስለ አሳየ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ 5በስሙ እንዲያምኑ አሕዛብን ልናስተምር ሐዋርያት ተብለን የተሾምንበትና ጸጋን ያገኘንበት፥ 6እናንተም ዛሬ በኢየሱስ ክርስቶስ ለማመን እንደ ተጠራችሁ። 7በሮሜ ላላችሁ፥ እግዚአብሔር ለሚወዳችሁ፥ ለመረጣችሁና ላከበራችሁ ሁሉ፥ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን።
8አስቀድሜ ስለ ሁላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፤ ማመናችሁ በዓለም ሁሉ ተሰምታለችና። 9ባለማቋረጥ በምጸልየው ጸሎት እንደማስባችሁ ልጁ በአስተማረው ወንጌል በፍጹም ልቡናዬ የማመልከው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። 10ወደ እናንተ እመጣ ዘንድም እግዚአብሔር በፈቃዱ መንገዴን ያቃናልኝ ዘንድ ዘወትር እጸልያለሁ። 11ትጸኑ ዘንድ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ እንድታገኙ ላያችሁ እወዳለሁና፤ 12ይህንም ማለቴ በመካከላችን ባለች በእናንተና በእኔ እምነት አብረን በእናንተ እንድንጽናና ነው። 13#የሐዋ. 19፥21። ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ፥ በሌሎች አሕዛብ እንደ ሆነ በእናንተም ዋጋዬን አገኝ ዘንድ ሁልጊዜ ወደ እናንተ ልመጣ እንደ ወደድሁ፥ እስከ ዛሬ ድረስም እንደ ተሳነኝ ልታውቁ እወድዳለሁ። 14ለአረማውያንና ላልተማሩ፥ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉም ሁሉ አስተምር ዘንድ ዕዳ አለብኝ። 15ይልቁንም በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ወንጌልን ላስተምራችሁ እተጋለሁ።
16 #
ማር. 8፥38። ወንጌልን ለማስተማር አላፍርምና፤ አስቀድሞ አይሁዳዊን፥ ደግሞም አረማዊን፥ የሚያምኑበትን ሁሉ የሚያድናቸው የእግዚአብሔር ኀይሉ ነውና። 17#ዕን. 2፥4። “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ብሎ መጽሐፍ እንደ ተናገረ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና።
በኃጥኣን ላይ ስለሚመጣው መቅሠፍት
18እውነትን ዐውቀው በክፋታቸው በሚለውጡአት በዐመፀናውና በኀጢአተናው ሰው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ከሰማይ ይመጣል። 19እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው እግዚአብሔርን ማወቅ በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና። 20የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኀይሉና ጌትነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ የፈጠረውን ፍጥረት በማሰብና በመመርመር ይታወቃል፤ መልስ የሚሰጡበትን ምክንያት እንዳያገኙ። 21#ኤፌ. 4፥17-18። እግዚአብሔርን ሲያውቁት እንደ እግዚአብሔርነቱ አላከበሩትም፤ አላመሰገኑትምም፤ ነገር ግን ካዱት፤ በአሳባቸውም ረከሱ፤ ልቡናቸውም ባለማወቅ ጨለመ። 22ጥበበኞች ነን ሲሉ አላዋቆች ሆኑ። 23#ዘዳ. 4፥16-18። የማይሞተውን የእግዚአብሔርን ክብር በሚሞት ሰውና በዎፎች፥ አራት እግር ባላቸውም፥ በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ።
24ስለዚህም እግዚአብሔር እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵሰት አሳልፎ ተዋቸው። 25የእግዚአብሔርን እውነት ሐሰት አድርገዋታልና፤ ተዋርደውም ፍጥረቱን አምልከዋልና፤ ሁሉን የፈጠረውን ግን ተዉት፤ እርሱም ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ ነው፤ አሜን።
26ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ መቅሠፍትን አመጣባቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ትተው ለባሕርያቸው የማይገባውን ሠሩ። 27ወንዶችም እንዲሁ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን ትተው በፍትወት ተቃጠሉ፤ እርስ በርሳቸውም እየተመላለሱ፥ ወንዶች በወንዶች ላይ የሚያዋርዳቸውን ነውር ሠሩ፤ ነገር ግን ፍዳቸውን ያገናሉ፤ ፍዳቸውም በራሳቸው ይመለሳል። 28እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱ መጠን እንዲሁ እግዚአብሔር ይህን የማይገባውን ይሠሩ ዘንድ ሰነፍ አእምሮን ሰጣቸው። 29እነርሱም ዐመፅን ሁሉ፥ ክፋትንም፥ ምኞትንም፥ ቅሚያንም፥ ቅናትንም የተመሉ ናቸው፤ ምቀኞች፥ ነፍሰ ገዳዮች፥ ከዳተኞች፥ ተንኰለኞች፥ ኩሩዎች፥ ጠባያቸውንና ግብራቸውንም ያከፉ ናቸው። 30ሐሜተኞች፥ እግዚአብሔርን የሚጠሉ፥ ተሳዳቢዎች፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክሕተኞች፥ ክፋትን የሚፈላለጉ፥ ለወላጆቻቸውም የማይታዘዙ ናቸው። 31የማያስተውሉ፥ ዝንጉዎች፥ ፍቅርም፥ ምሕረትም የሌላቸው ናቸው። 32ይህን እንዲህ ላደረገ ሞት እንደሚገባው እነርሱ ራሳቸው የእግዚአብሔርን ፍርድ እያወቁ፥ እነርሱ ብቻ የሚያደርጉት አይደለም፤ ነገር ግን ሌላውን ያነሣሡታል፤ ያሠሩታልም።
Currently Selected:
ወደ ሮሜ ሰዎች 1: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in