መዝሙረ ዳዊት 113
113
ሃሌ ሉያ።
1እስራኤል ከግብፅ፥
የያዕቆብም ወገን ከጠላት ሕዝብ በወጡ ጊዜ፥
2ይሁዳ መመስገኛው፥
እስራኤልም ግዛቱ ሆነ።
3ባሕር አየች፥ ሸሸችም፥
ዮርዳኖስም ወደኋላው ተመለሰ።
4ተራሮች እንደ ኮርማዎች፥
ኮረብቶችም እንደ በጎች ጠቦቶች ዘለሉ።
5አንቺ ባሕር የሸሸሽ፥
አንተም ዮርዳኖስ ወደ ኋላህ የተመለስህ፥ ምን ሁናችሁ ነው?
6እናንተም ተራሮች፥ እንደ ኮርማዎች፥
ኮረብቶችስ፥ እንደ በጎች ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ?
7ከያዕቆብ አምላክ ፊት፥
ከእግዚአብሔር ፊት ምድር ተናወጠች፤
8ዐለቱን ወደ ውኃ ምንጭ፥
ባልጭቱንም ወደ ውኃ ኩሬ የለወጠ።
9 # በዕብ. መዝ. 115 ነው። ለእኛ አይደለም፥ አቤቱ፥ ለእኛ አይደለም፥
ነገር ግን ለስምህ፥
ስለ ምሕረትህና ስለ እውነትህም ምስጋናን እንስጥ#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ስጥ” ይላል።
10አሕዛብ፥ “አምላካቸው ወዴት ነው?” አይበሉ።
11አምላካችንስ በላይ በሰማይ ነው፤
በሰማይም በምድርም፥
እግዚአብሔር#“እግዚአብሔር” የሚለው በግእዝ ብቻ። የፈቀደውን ሁሉ አደረገ።
12የአሕዛብ ጣዖታቶች የወርቅና የብር፥
የሰው እጅ ሥራ ናቸው።
13አፍ አላቸው ግን አይናገሩም፤
ዐይን አላቸው ግን አያዩም፤
14ጆሮ አላቸው ግን አይሰሙም፤
አፍንጫ አላቸው ግን አያሸትቱም፤
15እጅ አላቸው ግን አይዳስሱም፤
እግር አላቸው ግን አይሄዱም፤
በጉሮሮአቸውም አይናገሩም።
16በአፋቸው ትንፋሽ የለም፥#“በአፋቸው ትንፋሽ የለም” የሚለው በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
የሚሠሩአቸውም የሚያምኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ።
17የእስራኤል ወገኖች ሆይ፥ በእግዚአብሔር ታመኑ፤
ረዳታቸውና መታመኛቸው እርሱ ነው።
18የአሮን ወገኖች ሆይ፥ በእግዚአብሔር ታመኑ፤
ረዳታቸውና መታመኛቸው እርሱ ነው።
19እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ታመኑ፤
ረዳታቸውና መታመኛቸው እርሱ ነው።
20እግዚአብሔር ሆይ፥ አስበን ባርከንም#ዕብ. “ዐሰበን ይባርከናልም” ይላል።
የእስራኤልንም ወገኖች ባርክ፥ የአሮንንም ወገኖች ባርክ።
21እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥
ትንንሾችንና ትልልቆችን ሁሉ ባርካቸው።#ዕብ. “ይባርካል” ይላል።
22እግዚአብሔር በላያችሁ፥
በላያችሁና በልጆቻችሁ ላይ ይጨምር።
23እናንተ ሰማይንና ምድርን ለሠራ
ለእግዚአብሔር የተባረካችሁ ናችሁ።
24የሰማዮች ሰማይ ለእግዚአብሔር ነው፤
ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጠ።
25አቤቱ፥ ሙታን የሚያመሰግኑህ አይደሉም፥
ወደ ሲኦልም የሚወርዱ ሁሉ፤
26እኛ ሕያዋን ግን ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም
እግዚአብሔርን እናመሰግናለን።
Currently Selected:
መዝሙረ ዳዊት 113: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in